AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የሎጀስቲክስና የኮሙኒኬሽን አቅም የሀገራትን ዕድገትና ተፅዕኖ የሚወስን መሠረታዊ ኃይል ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመተባበር ለቀናት ሲያካሂድ የቆየው የአፍሪካ የሎጂስቲክስና የኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም ተጠናቋል።
በሲምፖዚየሙ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤በታሪክ ውስጥ የሀገራት እድገትና ተፅዕኖ የተወሰነው በኢኮኖሚያቸው ጥንካሬ ወይም በጦር ኃይላቸው መጠን ብቻ ሳይሆን በሎጀስቲክስ ሥርዓታቸው ውጤታማነትና በኮሙኒኬሽን አቅማቸው ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘመናዊው ዓለም ፍጥነት፣ ትክክለኛነት፣ አስተማማኝነትና አብሮ የመሥራት ብቃት ወሳኝ ጥቅሞች መሆናቸውን ገልፀው ሎጀስቲክስ አንድ ሀገር ራሷን የምታስቀጥልበትን፣ ሀብቷን የምታንቀሳቅስበትን፣ ተፅዕኖዋን የምታስፋፋበትንና በችግር ጊዜ ጽናቷን የምትጠብቅበትን አቅም የሚወስን መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሙኒኬሽን ደግሞ መረጃን ለመሰብሰብ፣ ቅንጅትን ለማስቀጠል፣ ውሳኔን ለመደገፍና የጋራ ጥረትን ለማረጋገጥ መሠረታዊ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

የትጥቅ ግጭቶች፣ የሳይበር ጥቃቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በአቅርቦት ሰንሰለት የሚፈጠሩ መቋረጦች፣ ወረርሽኞችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሎጀስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሚና ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።

የአፍሪካ ደህንነትና ብልጽግና ትብብርን በማጠናከር፣ ፈጠራን በማበረታታት፣ አብሮ የመሥራት አቅምን በማሳደግ፣ እውቀትን በመጋራትና የጋራ አቅምን በመገንባት ላይ እንደሚመሰረት ጠቁመው አፍሪካ አምራች የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ እያደጉ ያሉ ገበያዎችና ሰፊ የእድገት ዕድሎች እንዳሏት ገልጸዋል።
በተቋማት ላይ በመዋዕለ ንዋይ በማፍሰስና የቴክኖሎጂ ለውጥን በመቀበል ለዘላቂ ሰላም፣ ደህንነትና ብልጽግና ጠንካራ መሠረት መጣል እንደሚቻል በመግለጽ ኢትዮጵያም ለእነዚህ ዓላማዎች በፅናትና በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል አብዱራህማን እስማኤልን ጨምሮ የአፍሪኮም ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ተገኝተዋል።