በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና የመልሶ ማልማት ስራዎች፣ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀች እያደረጓት ነው

You are currently viewing በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና የመልሶ ማልማት ስራዎች፣ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀች እያደረጓት ነው
  • Post category:ልማት

AMN – መጋቢት 26/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማትና የመልሶ ማልማት ስራዎች፣ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀች እያደረጓት መሆኑን ጎብኚዎች ገለጹ።

ከትግራይ ክልል ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ጐብኝዎች፤ በከተማዋ የተገነቡ መጠነ-ሰፊ የልማት ስራዎችንና የአድዋ ድል መታሰቢያን ተዘዋውረው በመጎብኘት የታዘቡትን አስደናቂ ለውጥ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።

ከተማዋ ከዚህ ቀደም ከነበረችበት ሁኔታ በእጅጉ መለወጧን የገለጹት ወ/ሮ ሲሳይ ባዬ፣ አሁን ላይ አዲስ አበባ የአውሮፓን ደረጃ የያዘች ዘመናዊ ከተማ እየሆነች መሆኑን መስክረዋል።

ቀደም ሲል ለነዋሪዎች ምቹ ያልነበሩና የቆሻሻ ክምችት ይታይባቸው የነበሩ እንደ “ዶሮ ማነቂያ” ያሉ ሰፈሮች፣ አሁን ላይ በሚገርም ሁኔታ ተገንብተውና ጽዱ ሆነው ለከተማዋ ልዩ ውበት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው ጐብኝ አቶ መሐመድ ጀማል በተመሳሳይ መልኩ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች አካባቢውን ከነበረበት መጥፎ ሽታ በማጽዳት፣ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ታሪክ እና የአባቶችን ጀግንነት የሚዘክር ትልቅ አሻራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ሄኖክ ግደይ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ የታየው የልማት ተሞክሮ ወደ ትግራይ ከተሞችም ተስፋፍቶ ማየት ምኞታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ መቐለ፣ ዓዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ እና ዓድዋ ያሉ ከተሞችም ተመሳሳይ የኮሪደር ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና ወጣቶች በዚህ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው፣ ጉብኝቱ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመው፣ ጎብኚዎቹ ለሰላምና ለልማት ያላቸውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ በከተማዋ የታየው ለውጥ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች እንደ ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድ ነውም ብለዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review