የንስርን ከፍታ በመላበስ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የንስርን ከፍታ በመላበስ የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ትርጉም ዬለሽ ትንኮሳዎችና መሰናክሎች ወደ ጎን በመተው ፣ ትኩረቷን በትልልቅ ሀገራዊ ህልሞች ላይ በማድረግ የብልጽግና ጉዞዋን እንደምታፋጥን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል የተገነባውን የሐሮ ደንዲ ኢኮ ሎጅ ምርቃን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፣ በንስር እና በቁራ መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ባህሪ በምሳሌነት ጠቅሰው ፣ ሀገራዊ ስኬትን ለማረጋገጥ ትኩረትን በከፍታና በታላቅ ህልም ላይ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ንስር በተፈጥሮው አርቆ የሚያይ፣ ብርቱና በከፍታ ላይ የሚመላለስ የአእዋፍ ንጉሥ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቁራ ደግሞ በተቃራኒው በዝቅታ የሚበር እና ንስርን በመሬት ላይ ሲያገኝ አንገቱ ላይ ወጥቶ ለመተናኮል የሚሞክር የአእዋፍ ዝርያ መሆኑን ገልጸዋል።

ንስሩ ግን ለቁራው ትንኮሳ ምላሽ በመስጠት ጊዜውን እንደማያባክን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቁኑ ወደ ተፈጥሯዊ ከፍታው በከፍተኛ ፍጥነት በመምዘግዘግ ወደ ላይ በወጣ ቁጥር ቁራው ከፍታውን መቋቋም አቅቶት በራሱ ጊዜ እንዲፈጠፈጥ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።

ይህንን ተፈጥሯዊ ምሳሌ ወደ ሀገራዊ እውነታው ያመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያም የሚያጋጥሟትን መሰናክሎችና ጩኸቶች ወደ ጎን በመተው፣ እንደ ንስር ወደ ከፍታዋ በመብረር የታለመላትን ብልጽግና እንደምታረጋግጥ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ የንስር አይነት እይታ ያላቸው ሰዎች በያዙት የከፍታ መንገድ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ከተጓዙ ትርጉም የሌላቸው ትንኮሳዎች በራሳቸው ጊዜ እንደሚወድቁ ገልጸዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review