AMN- ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም
የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የከተማዋ ነዋሪዎች ምቹና ቀልጣፋ የማዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ በበዓል ወቅት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሁሉም ዘርፎች የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የጥናትና ልማት ትግበራ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከተማ አስተዳደሩ በዓሉ በሰላም እንዲከበርና ነዋሪው አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ በቂ ዝግጅት አድርጓል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የጠቀሱት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፣ አስተማማኝ የጽዳት፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ያለምንም መስተጓጎል እንዲሰጡ የቅርብ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የአደጋ መከላከል ሥራን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ በዓሉ አደጋ ሳይከሰት በሰላም እንዲጠናቀቅ በሰው ኃይልና በግብዓት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በአስራ አንዱም ቅርንጫፎች ሙሉ ዝግጅት መደረጉንና ለህብረተሰቡም ቅድመ መከላከልን የተመለከቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት የኤሌክትሪክ መገልገያዎችንና ከሰል ሲጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማስመልክት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ኃይለኢየሱስ ደህናነው በበዓሉ ወቅት በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ ከውሃና ፍሳሽ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ችግር ሲገጥመው በ906 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠት እንደሚችልም አመልክተዋል።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅን የኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጂሳ ካሳ፤ በበዓሉ ወቅት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና ብልሽቶች ሲከሰቱም በፍጥነት ለመጠገን የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ ሽኩር በበኩላቸው፤ በበዓል ወቅት የሚፈጠረውን የደረቅ ቆሻሻ ወይም ተረፈ ምርት በአግባቡ ለመሰብሰብና ከተማዋን ጽዱ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን በመጥቀስ ህብረተሰቡ ንጽህናው በተጠበቀ አካባቢ በዓሉን እንዲያከብር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በቴዎድሮስ ይሳ