AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ታሪካዊ መብት ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ፍላጎትና የቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካይ እና የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባል አቶ ከማል ሃሺ መሐሙድ ገለጹ።
አቶ ከማል ሃሺ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፤ የባህር በር ለኢትዮጵያ ለገቢና ወጪ ንግዷ እንዲሁም ለሀገራዊ ደህንነቷ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህ የባህር በር ፍላጎት በሰላማዊ መንገድና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፤ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የባህር በር ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የምክር ቤት አባሉ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባህር በር፤ ለብቻዋ ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማትና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፍላጐቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የተከተለና የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት በማይነካ መልኩ የቀረበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከማል፤ ግቡ በጋራ ስምምነትና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚሳካ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ብትሆን በአፍሪካ ቀንድ የሚታየውን የንግድ ፍሰት ከማሳለጡ ባለፈ፤ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በመሆኑም መንግስት ይህንን ስትራቴጂካዊ ግብ ለማሳካት ከአጋር ሀገራት ጋር የሚያደርገውን የዲፕሎማሲ ንግግር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በበረከት ጌታቸው