AMN- ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ መዲና የሆነችዉ አዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ያስመዘገበችዉና በማስመዝገብ ላይ የምትገኘዉ ፈጣን እድገት እና አስተማማኝ ሰላም የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነዉ፡፡
የከተማዋን ነዋሪዎችና ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የሀገሪቱን ዜጎች ጨምሮ ባህር ተሻግረዉና ድንበር አቋርጠዉ የመጡ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች፤ ታወቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ቱሪስቶች ስለ አዲስ አበባ ፈጣን ልማትና እድገት ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች በመመስከር ላይ ይገኛሉ፡፡
አንዳንድ የአፍሪካ እና የሌሎች የዓለም ሃገራት መሪዎች መዲናዋ በሁሉም ዘርፎች ያስመዘገበቻቸዉን ለዉጦች ከማወደስ አልፈዉ ልዑካኖቻቸዉን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ተሞክሮዉን እስከመቀመርና ወደ ሃገራቸዉ እስከመዉሰድ ደርሰዋል፡፡
ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችና ኩነቶች ወደ አዲስ አበባ የመጡ እንግዶችም በመዲናዋ ፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ከመደነቅ አልፈዉ ቆይታቸዉን አራዝመዋል፤ አዲስ አበባን ያላዩ ሌሎች ጓደኞቻቸዉም አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ጥሪ እስከማስተላለፍ ደርሰዋል፡፡

ዘመኑ በፈጠራቸዉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የአዲስ አበባን ለዉጥና እድገት የተመለከቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም አዲስ አበባን ለመጎብኘት የወራትና የአመታት ጊዜ አልወሰደባቸዉም፡፡
ዩቲዩበሩ በዩቲዩብ፤ ቲክቶከሩ በቲክቶክ፤ ፎቶ ግራፍ አንሺዉ በካሜራዉ ሌሎችም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ስለ አዲስ አበባ ዉብ አበባነት፤ ልማትና እድገት፤ ቀንና ምሽት፤ በቀጥታ ስርጭት ጭምር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዓለም ህዝቦች አሰራጭተዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ሃገር፤ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የአዲስ አበባን ፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ደግመዉ ደጋግመዉ ዘግበዋል፡፡
ስለ አንድ ሃገር ልማት፤ ስለ ህዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና መሰል አዎንታዊ ጉዳዮች በአደባባይ መመስከር እምብዛም ባልተለመደበት ዘመን ላይ በርካቶች ይህንን አሉታዊ አጥር ሰብረዉ የአዲስ አበባን ፈጣን ልማት እድገት ለዓለም መስክረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያለፉትን የለዉጥ አመታት ጨምሮ በተለይ በበጀት አመቱ 9 ወራት በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ በርካታ ተግባራትን አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ የከተማም ሆነ የአንድ ሃገር ልማት የሚጀምረዉ ከሃሳብ ፖለቲካ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ባልተለወጠ የፓለቲካ እሳቤና ባህል ሃገር መገንባት አይቻልም ያሉት ከንቲባዋ ኢትዮጵያን ለዘመናት ወደኋላ ያስቀራትም ይህዉ ያልተለወጠ እሳቤ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከለዉጡ በኋላ አዲስ አበባን እንደስሟ ዉብ አበባ ለማድረግ የገባዉን ቃል ለመተግበር ወደ ስራ ሲገባ የመንግስትን የልማት እቅድ የሚያጣጥሉ፤ የማያራምዱና የማያሰሩ በርካታ እንቅፋቶች፤ አሉባልታዎች፤ ዘመቻዎችና ለዘመናት የተለመዱ አዙሪቶች መከሰታቸዉን አስታዉሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የለዉጡ አመራር ልዩነቶችን አክብሮ በጋራ በመስራትና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ባደረገዉ ጥረት አሁን ላይ በርካታ ዉጤቶች ተመዝግበዋል፤ አዲስ አበባም ዋንኛ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለመሆን በቅታለች፡፡
ባለፉት የለዉጥ አመታት በርካታ ፈተናዎች፤ የጥላቻ አጀንዳዎችና የተሳሳቱ ትርክቶች በስፋት ቢከሰቱም ፈተናዎቹን በጽናት አልፈን በሁሉም ዘርፎች አመርቂ ዉጤቶችን አስመዝግበናል ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ