AMN – ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም
ከዓመት በፊት በሰው ልጆች እና በሮቦቶች መካከል በተጀመረው የሩጫ ውድድ ሮቦቶች ቀርፋፋ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ሮቦቶች የታሪክ አቅጣጫን የሚቀይር አዲስ ምዕራፍ ላይ በመድረሳቸው በሩጫ የሰውን ልጅ በመቅደም በርቀቱ ታሪካዊ ሪከርድ ማስመዝገብ ችለዋል።
በቤጂንግ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር፣ “ላይትኒንግ” የተሰኘው የቻይና ሰው መሰል ሮቦት በሰው ልጅ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በመስበር ውድድሩን አንደኛ ሆኖ አጠናቋል።
በቻይናው ሆነር የስማርት ስልክ አምራች ኩባንያ የተሰራው ይህ ሮቦት፣ 21 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ርቀት የቤጂንግ ግማሽ ማራቶን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ 50 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ብቻ ነበር።
አሸናፊው ሮቦት በኡጋንዳዊው አትሌት ያቆብ ኪፕሊሞ ተይዞ የነበረውን የ57 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ የዓለም ክብረ ወሰን ከ6 ደቂቃ በላይ የሆነ ልዩነት ማስመዝገቡ ተመላክቷል።
ይህ ቁመቱ 169 ሳንቲ ሜትር የሆነውና ደማቅ ቀይ ቀለም የተቀባው ሰው መሰል ሮቦት ሚዛኑን መጠበቅ እንዲያስችለው አጫጭር ክንዶቹን እያወዛወዘ ያለምንም ድካም ሩጫውን በአንደኝነት መጨረሱ ተገልጿል። ይህም ስኬት ቻይና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በምታደርገው ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ተነግሮለታል።

የቻይና መንግስት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ ሮቦቲክስን ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ እድገት ወሳኝ ከሆኑ 10 ዘርፎች አንዱ አድርጎ በመለየት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 2023 የወጣ የፖሊሲ ሰነድ ደግሞ ሰውን መሰል ሮቦቶችን ለማምረት የቴክኖሎጂ ፉክክር አዲስ ግንባታ መያዙን በመጥቀስ በ2025 በስፋት ለማምረት ግብ አስቀምጧል።
የቻይና መንግስት ባስቀመጠው የትኩረት አቅጣጫ መሰረት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሮቦት ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።
በዘንድሮው የሰውን መሰል ሮቦት ግማሽ ማራቶን ላይ ከ100 በላይ ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ ብልጫ አለው።
ላይትኒንግ የተባለው ሮቦት ካለፈው ዓመት ሻምፒዮን ሮቦት በሁለት ሰዓት የሚበልጥ ፈጣን ጊዜ አስመዝግቧል።
በሰዎች ምድብ ወንዶች ዣኦ ሃይጂ እና ከሴቶች ደግሞ ዋንግ ኪያኦክሲያ የተባሉ ሯጮች ያሸነፉ ሲሆን፣ ሁለቱም ውድድሩን ለመጨረስ ከአንድ ሰዓት በላይ ፈጅቶባቸው እንደነበር የሲ ኤን ኤን ዘገባ ያመላክታል።
ይህ የሮቦቶች በስፖርት ሜዳ ላይ መፋለም፣ በቴክኖሎጂው ዓለም የወደፊት አቅጣጫ ላይ አዲስ የውይይት አጀንዳ ሊከፍት እንደሚችልም ይጠበቃል።
በወርቅነህ አቢዮ