አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ቦታ እየኖሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ግጭት የሚያራግቡ ግለሰቦች ከድርጊታቸዉ ሊቆጠቡ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ቦታ እየኖሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ግጭት የሚያራግቡ ግለሰቦች ከድርጊታቸዉ ሊቆጠቡ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN—ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ቦታ እየኖሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ግጭት የሚያራግቡ ግለሰቦች ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየደረገ ያለዉን ጥረት እና በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ግጭቶች የሚፈጠሩባቸዉን ምክንያቶች በስፋት ዘርዝረዋል፡፡

ብሄር፤ ሃይማኖት እና ርዕዮተ አለምን መነሻ አድርገዉ የሚፈጠሩ ግጭቶች መኖራቸዉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማግኘት፤ የበላይነትን ለማስፈን እና ግዛትን ለማስፋፋት በሚደረጉ ጥረቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች መኖራቸዉን አንስተዋል፡፡

የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማግኘት፤ የበላይ ለመሆን እና ግዛት ለማስፋፋት በይፋ ግጭት ዉስጥ የሚገቡ አካላት ባይኖሩም ይህንን ፍላጎቶቻቸዉን ለማስፈጸም የሚጠቀሙት የብሄር እና ሃይማኖት አጀንዳዎችን መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሁሉም ሃይማኖቶች የሰላም እንጂ የግጭት አላማ የላቸዉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃይማኖትን ለግጭት አላማ የሚጠቀሙ ሃይሎች መኖራቸዉንም ገልጸዋል፡፡

በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ምንም አይነት የሃይማኖትም ሆነ የብሄር ግጭት እንደሌለ መረጃዎችን ጠቅሰዉ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ነዉጠኞች ግን በተለያዩ አካባቢዎች የሃይማኖትና የብሄር ግጭት እንደሚለኩሱ ተናግረዋል፡፡

ነዉጠኞቹ የሚለኩሱትን እሳት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያራግቡ አካላት ጉዳዩን የሚዘግቡበትና የሚያሰራጩበት መንገድ አግባብነት የሌለዉና ሃገር አፍራሽ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አሜሪካዊያን ከመንግስታቸዉ በላይ ለሃገራቸዉ መከላከያ ሰራዊት ትልቅ ክብር እንዳላቸዉና ይህም የስልጣኔ ምልክት መሆኑን በምሳሌነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየሞቱና ዋጋ እየከፈሉ ሃገር ለሚያጸኑ የጸጥታ አካላት ክብር መስጠት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

7ኛዉን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች በአርሲ ዞን የፈጸሙትን ጥቃት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የአካባቢዉ ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች በንጹሃን ዜጎች ላይ ሊፈጸም የነበረዉን ጥፋት ለመከላከል የህይወት መስዋእትነት እስከመክፈል መድረሳቸዉን በመግለጽ ለእነዚህ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ክብር መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በወቅቱ የተፈጠረዉን ግጭት የብሄር እና የሃይማኖት መልክ ለማስያዝ የሞከሩ ሃይሎች ቢኖሩም በአካባቢዉ የሚኖሩ የሙስሊም እምነት ተከታዮችና የጸጥታ አካላት ግን ህዝቡን ከጸረ ሰላም ሃይሎች ለመታደግ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

የብሄርና የሃይማኖት ግጭቶችን በማራገብ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ሊኖር አይገባም፤ የሞተዉ ወንድማማች ህዝብ ነዉ፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ቦታ ላይ እየኖሩ፤ የተፈጠረዉን ችግር በአግባቡ ሳይረዱ ግጭት የሚያራግቡ አካላት ከድርጊታቸዉ ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በሰላማዊ ቦታ ሆነዉ ግጭት የሚያባብሱ ግለሰቦችን እና በየአካባቢዉ እየተንቀሳቀሱ ግጭት የሚፈጥሩትን አካላት ለይተን አናይም ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምንም አይነት በቂ መረጃ ሳይኖራቸዉ ብሄርን ከብሄር፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ ሃሰተኛ መረጃዎች ከማሰራጨት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review