በቀጣይ በአምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች ይገነባሉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በቀጣይ በአምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች ይገነባሉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN -ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመኖሪያ ቤት ችግርን ስለመቅረፍ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፣ መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን መገንባት እንደቻለ በማብራሪያቸው አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ አዲስ የግንባታ ቴክኖሎጂንና የረጅም ጊዜ የቤት ብድር ሥርዓትን በማስተዋወቅ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ የቤት ልማት ፖሊሲ ተቀርጾ በካቢኔ መጽደቁንና በሁሉም ክልሎች የተቀናጀ ንቅናቄ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ግንባታው በመንግሥት በጀት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነት መዋቅሮችን በስፋት መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች ግንባታውን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራውን ጠቅሰዋል፡፡

የዜጎችን የመግዛት አቅም ያገናዘበና ፍላጎታቸውን የሚያስተናግድ አዲስ የፋይናንስ አሠራር መፈጠሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ሰዎች ቤት በቀጥታ መግዛት ካልቻሉ በመንግሥት በሚመቻቸው አዲስ የሞርጌጅ ሥርዓት አማካኝነት ከገቢያቸው ላይ እየከፈሉ በረጅም ጊዜ ሂደት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review