AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስለሀብት አጠቃቀም እና ለፕሮጀክቶች የሚሆን የገንዘብ አቅም በማሳደግ ረገድ በሰጡት ማብራሪያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ አሰባሰብ መሻሻል እንደታየበት ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ክልሎች ከፌደራል መንግስት የሚፈስ ሀብትን ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸውን ገቢ ማሳደግ እንዳለባቸው ነው በማብራሪያቸው የገለጹት፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከለውጡ በፊት ይሰበሰብ የነበረው ገቢ በጣም ያሳፍር ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘንድሮ ግን 340 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
340 ቢሊየን ብር ከለውጡ በፊት የፌደራል መንግስት እንኳን የማያስገባው እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
የመስረተ ልማት ግንባታዎችን በሚመለከት በሰጡት ገለጻም፣ በአዲስ አበባ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው