AMN – ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸዉን ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት አመት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የጤና ዘርፉን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ፣ መዲናዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተጀመረው ሥራ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ አራት አዳዲስ ሆስፒታሎችን መገንባት ተችሏል።
እነዚህም የአበበች ጎበና፣ የላፍቶ፣ የቤተል መንዲዳ እና የገላን ትሮማ ሴንተር መሆናቸው ገልጸው ሁለቱ ሆስፒታሎችም በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የተገነባው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ብቻ እንደነበረ በማስታወስ አሁን የተመዘገበው ዉጤት የሚበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ የጤና አገልግሎትን ከማሻሻልና የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ለሕክምና የሚወጣውን ወጪ ለማስቀረት በርካታ ስራዎችን መስራቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ነባር ሆስፒታሎች እንደ አዲስ እንዲደራጁ መደረጉን ገልጸው ከእነዚህም መካከል የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የአልጋ አቅሙን በእጥፍ በማሳደግ የግል ሆስፒታል ሊሰጠው ከሚችለው በላይ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች ተሟልተውለት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
እንዲሁም በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ባለ 5 ወለል ህንጻ ተገንብቶ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ነጻ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትልቁና የመጀመሪያው የሆነው የአይን ህክምና ማዕከል እና የዲ ኤን ኤ ምርመራ የሚያካሄድበት የፎረንሲክ ሴንተር ተገንብቶ ግብዓቶች እየተሟሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የራስ ደስታ ሆስፒታል የራሱን ኦክስጅን ማምረት የሚችልበትን አቅም ከመፍጠር ባለፈ ለሌሎች ሆስፒታሎች ኦክስጅን ለማከፋፈል የሚያስችል ስራ መስራቱን የገለጹት ከንተባ አዳነች አቤቤ ሆስፒታሉን ወደ ርሆቦቲክስ የቀዶ ጥገና ህክምና ለማድረስ ታልሞ እየተሰራ መሆኑ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ የጤና ጣቢያዎች ደረጃቸው ተሻሽሎ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ በትላልቅ ሆስፒታሎች ላይ የሚደርሰዉን መጨናነቅ እንደቀነሰ አብራርተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት 9 ወራት የተከናወኑ ስራዎች በጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥባት ከተማ ለማድረግ የተያዘው ግብ አካል መሆኑንም አብራርተዋል።
በትዝታ መንግሥቱ