የናፍጣ አቅርቦት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት መጠን እንዲመለስ ተወሰነ

You are currently viewing የናፍጣ አቅርቦት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት መጠን እንዲመለስ ተወሰነ

AMN – ሚያዝያ 21/ 2018 ዓ.ም

የናፍጣ አቅርቦት ከመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በፊት ወደነበረበት የአቅርቦት መጠን እንዲመለስ መንግስት መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት ወቅታዊ ሁኔታውን ገምግሞ ውሳኔውን ያስተላለፈው ሀገሪቱ አሁን ላይ በከፍተኛ የግብርና እና የምርት እንቅስቃሴ ላይ በመገኘቷ እንዲሁም የትራንስፖርት ችግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አስታውቀዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት በቀን 9 ሚሊዮን ሊትር የነበረው የናፍጣ አቅርቦት በግማሽ ቀንሶ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ሆኖ መቆየቱን ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ ከዛሬ ጀምሮ ግን እንደ ቀድሞው በቀን 9 ሚሊዮን ሊትር ለማቅረብ መወሰኑን ገልጸዋል።

የስርጭት ሂደቱን በተመለከተም፦ ለአዲስ አበባ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ከጅቡቲ ማጓጓዝ እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን፣ ለክልሎች ደግሞ ከነገ ጀምሮ ማጓጓዝ እንደሚጀመር አቶ አህመድ ሽዴ አብራርተዋል።

መንግስት ከጦርነቱ በፊት ለነዳጅ ሲያደርገው ከነበረው የ10 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ድጎማ በተጨማሪ፣ በአሁኑ ወቅት በአመት 20 ቢሊዮን ብር እየደጎመ መሆኑ ተገልጿል።

ይህም በአጠቃላይ የነዳጅ ድጎማ መጠኑን ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲደርስ አድርጎታል።

ይህ እርምጃ መንግስት የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል እና የምርትና ምርታማነት ሂደት እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑ ተመልክቷል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review