AMN- መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ጨፌ ኦሮሚያ 7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ አመት አንደኛ ጉባኤውን በነገው እለት ማካሄድ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰአዳ አብዱረህማን ህዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የሰጣቸው የክልል ምክር ቤት ተወካዮች የመጀመሪያ የስራ ዘመናቸውን የሚጀምሩበት ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።
ለአዳዲስ የምክር ቤት አባላት አጠቃላይ በምክር ቤቱ ደንብና መመሪያ ላይ ስልጠና ሲሰጥ እንደነበረም አስታዉቀዋል።
ይህን ጉባኤ የክልሉ ህዝብ አዲስ መንግስት ለመመስረት በጉጉት ሲጠብቀው ቆይቷል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፣ የተለያዩ ሹመቶች የሚጸድቁበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የቀጣይ የክልሉ የስራ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ይቀመጣልም ብለዋል።
ባለፉት 5 አመታት የታዩ ክፍተቶች በጥናት ተለይተው ለመፍታት አቅጣጫ የሚቀመጥባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲሱ ምክር ቤት ህዝብ የሰጠውን አደራ ለመወጣት ትልቅ ስራ እንደሚጠብቀውም ወ/ሮ ሰአዳ ተናግረዋል።
በሔኖክ ዘነበ