የአንድነት፣ የባህል ቅብብሎሽና የማህበራዊ ትስስር ማጠናከሪያ – የመስቀል በዓል

AMN – መስከረም 17/2019 ዓ.ም

እንደ መስቀል ደመራ ያሉ ታላላቅ የአደባባይ በዓላት የጋራ ማንነትን በመገንባት፣ በቃልና በተግባር ባህልን ለትውልድ እንደሚያሻግሩ የቱሪዝም ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

የቱሪዝም ተመራማሪው ዶ/ር አያሌው ሲሳይ እንደገለጹት፣ በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘት ቢኖረውም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ባዳበራቸው የሰላም እና የጋራ እሴቶች አማካኝነት ማሕበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ይህ ባህላዊ መስተጋብር ታሪክን ፣ ዝማሬን እና ሌሎች የባህል መገለጫዎችን ከማስጠበቁም በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ዶ/ር አያሌው የገለጹት።

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን ይህን ታላቅ በዓል በአግባቡ በማስተዋወቅ የዓለም ህዝብ እንዲታደመው ማድረግ እንደሚገባም ተመራማሪው አሳስበዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ሃሳባቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም፣ መስቀል ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የፍቅር፣ የደስታ እና የሰላም መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ የሆነችው ትዕግስት መኮንን በመስቀል አደባባይ የሚታዩ ባህላዊ አልባሳት፣ የህዝብ አንድነት እና የደመራው ስነ-ሥርዓት ለኢትዮጵያውያን ልዩ ክብር የሚሰጠው የጋራ ደስታ መሆኑን ተናግራለች።

ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ መላክ ማይክል በበኩሉ፣ በዓሉ ከዘመድ አዝማድና ከጎረቤቶች ጋር ሰላም የሚታደስበት፣ የመሃል ሀገር ሰው ወደ ገጠር አቅንቶ ቤተሰቡን የሚጠይቅበት እንዲሁም የድሮ ጓደኞች የሚገናኙበት የትስስር ምዕራፍ መሆኑን አንስቷል።

አስተያየቱን ለኤ ኤም ኤን የሰጠው ፍቅሩ ስዩም ፣ የበዓሉ መምጣት የቤተሰብዊ ግንኙነት የሚጠናከርበት እና የገጠርና የከተማ ቁርኝት የሚታይበት ጊዜ መሆኑን ገልጿል።

የመስቀል ደመራ በዓል በየዓመቱ የኢትዮጵያውያንን ሕብረ-ቀለማዊነት፣ ፍቅርና አብሮነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያሻገር ታላቅ የሰላም እና የድምቀት መድረክ ሆኖ ቀጥሏል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review