AMN-መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ለሦስተኛ ጊዜ የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ሆናለች።
አትሌቷ ዛሬ በተካሄደው 52ኛው የበርሊን ማራቶን 2:11:04 በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት አጠናቃለች። አትሌቷ የዓለም ክብረወሰንን ለማሻሻል ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም።
ትዕግስት የውድድሩን አጋማሽ በዓለም ክብረወሰን ፍጥነት ብትጨርስም ወደ መጨረሻ አካባቢ የገጠማት መጠነኛ ጉዳት ህልሟን እንዳታሳካ አድርጓታል።

በውጤታማው አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ የምትሰለጥነው ትዕግስት አሰፋ ክብረወሰን ለማሻሻል እንደምትሞክር ከውድድሩ በፊት ገልፃ ነበር። ትግስት ምንም እንኳን የዓለም ክብረወሰን ባታሻሽልም የግል ምርጥ ሰዓቷን ግን ማስመዝገብ ችላለች።
አትሌቷ ከሦስት ዓመት በፊት በዚሁ በበርሊን ያስመዘገበችውን 2:11:53 ሰዓት በ49 ሰከንድ አሻሽላለች። ዛሬ ያስመዘገበችው ሰዓትም የምንግዜም 3ኛው ፈጣን ሰዓት ሆኗል።
በበርሊን ማራቶን ጥሩ ውጤት ያላት የ29 ዓመቷ አትሌት ከዚህ ቀደም በ2022 እና በ2023 ማሸነፏ ይታወሳል።
በውድድሩ በዳቱ ሂርጳ 2:16:53 በሆነ ሰዓት 2ኛ ስትወጣ ፣ 2:16:56 ሰዓት ያስመዘገበችው ደራ ዲዳ ደግሞ 3ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።
የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው የበርሊን ማራቶን በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 13 ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። ይህም ከየትኛውም ሀገራት አትሎቶች የበለጠ ነው።
በሸዋንግዛው ግርማ