AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የበጀት አመቱን 9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማን አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ መዛባትን ለመከላከል ስድስት ግዙፍ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን አስታዉቀዋል፡፡
ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ የገበያ ማዕከላትን መገንባት እንደማይቻል ተደርጎ ይወሰድ የነበረ ቢሆንም፤ አስተዳደሩ ባደረገው ጥናት መሠረት ምርት በብዛት ወደ ከተማዋ በሚገባባቸው አቅጣጫዎች ላይ እነዚህን ማዕከላት መገንባት ተችሏል።
ይህም ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ምርቶች በቀጥታ ለነዋሪው እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በዝርዝር ያቀረቡት ከንቲባዋ፣ በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ የተገነቡት ስድስት ማዕከላት ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአቅርቦት አማራጮችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 250 መድረሱን አስረድተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም፣ አስተዳደሩ ለዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ያለውን አጋርነት በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ ለትራንስፖርት፣ ለጤና መድህን፣ ለተማሪዎች ምገባና ለትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ድጎማ እንዲውል በየዓመቱ እስከ 18 ቢሊዮን ብር የሚደርስ በጀት በመመደብ የህዝቡን የኑሮ ወድነት ጫና ለመቀነስ በትጋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከድጎማው ጎን ለጎንም የገበያ ማዛባትንና ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የክትትል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ዝቅተኛ ገኒ ላላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች በራቸዉ ድረስ ገበያን ማቅረብ መቻሉን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸውን አዳዲስ አሰራሮችና የገበያ ማረጋጋት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
በበረከት ጌታቸው