አዲስ አበባ – የአፍሪካ የስፖርት ቱሪዝም አዲሷ ተመራጭ መዳረሻ

You are currently viewing አዲስ አበባ – የአፍሪካ የስፖርት ቱሪዝም አዲሷ ተመራጭ መዳረሻ

AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ በአፍሪካ ካሉ ምርጥ 10 ከተሞች ተርታ መሰለፏን ተከትሎ፣ በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ አዲስ የዕድል በር ተከፍቶላታል።

ከተማዋ በውበት፣ በንጽህና እና በዘመናዊ መሰረተ ልማቶች እያገኘችው ያለው ዓለም አቀፍ እውቅና፣ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ከለውጡ በፊት በከተማዋ የነበሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከ400 አይበልጡም ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን በመንግሥት፣ በባለሀብቱና በማህበረሰቡ የተቀናጀ ጥረት ከ2 ሺህ በላይ ዘመናዊ የስፖርት ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል። ይህ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከተማዋን በአፍሪካ ተመራጭ የስፖርት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕናቸውን እንዲገነቡ የሚያግዙ 114 ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 65ቱ ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ መገልገያዎች የተደራጁ መሆናቸውን ኃላፊው ከኤኤምኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አብራርተዋል።

ስፖርትን ከመሰረቱ (ከታችኛው እርከን) ለመጀመር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት ከ86 ሺህ በላይ ሰልጣኞች በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ የሥልጠና ሂደት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሰግደው፤ በቅርቡ በብሔራዊ ደረጃ ከተመረጡ 25 ታዳጊ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል 17ቱ ከአዲስ አበባ የተገኙ መሆናቸውን በምሳሌነት አንስተዋል።

በከተማዋ የተከናወነው የዋን ዴይ አትሌቲክስ ውድድር ያስመዘገበው ስኬትም፣ ለ2027ቱ ውድድር የወርቅ ደረጃ እንዲሰጠው ማስቻሉንም ገልጸዋል።

ሚያዝያ 24 እና 25 የማውንቴን ባይክ የብስክሌት ውድድር እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ሚያዝያ 26 አስር የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት የዞን 5 የእጅ ኳስ ውድድር ይካሄዳል ብለዋል።

በቀጣይ የአደይ አበባ እና የአቃቂ ስታዲየሞች፣ እንዲሁም ሌሎች የስፓርት ማዕከላት ሲጠናቀቁ አዲስ አበባ በአፍሪካ ቀዳሚ የስፖርት መዳረሻ ልትሆን እንደምትችል ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review