የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተባበረ ክንድ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን አከናውነው ታሪክ ጽፈዋል

AMN- ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

የከተማዋ ነዋሪዎች በተባበረ ክንድ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን አከናውነው ታሪክ ጽፈዋል ሲሉ የአዲስ አበባ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ገለጹ፡፡

አቶ ግርማ ሰይፉ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለፁት፣ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወነው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ህዝቡ በንቃት ተሳትፏል፡፡

ነዋሪዎች ዝናብና ብርድ ሳይበግራቸው በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በጋራ በመሆን ችግኞችን ሲተክሉ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሄም ኢትዮጵያውያን በአንድ ሀገራዊ ዓላማ ዙሪያ የሚተጉ ህዝቦች መሆናቸውን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 800 ሚሊየን ችግኞችን እንደ አዲስ አበባ ደግሞ ከ1 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የታለመው እቅድ መሳካቱን አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ጀምበር 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞች እንደተተከሉም በመግለጽ ለዚህም ነዋሪዎች ደማቅ አሻራቸውን አሳርፈዋል ብለዋል፡፡

የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአሁኑ ትውልድ ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች የነገዋን ውብ ሀገር ለመገንባት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸወን ጠቅሰው አረንጓዴ ዐሻራ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል በተጨማሪ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ በዛሬው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ የተሳተፉትንም አመስግነዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review