ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአንድነት በመትመም አዲስ ተዓምር ሠርተዋል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር 805.3 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል አዲስ ተዓምር መስራታቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለን መልእክት፤ ባለፉት የአረንጓዴ ዐሻራ ዓመታት ዛሬን በማሰብ ምግብ መመረቱን እና ለነገ ኃላፊነት ደግሞ ደን መለማቱን ገልጸዋል።

እንደ ሕዝብ የተጋነው ፍሬ አፍርቷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ተራሮች አረንጓዴ ካባ ደርበዋል፣ ወንዞች እንደገና መንጭተዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተራቆተወ ለብሶ፣ የጠፋው ተመልሶ፤ የደፈረሰው ጠርቶ፣ የነጠፈው አፍርቶ፤ የሀገር መልክ ተቀይሯል፤ ይሄንን ያየው ዓለምም ለትጋታችን ደጋግሞ ዕውቅና ሰጥቶናል ብለዋል፡፡

በራዕይ ማቀድን፣ በትጋት ወዳሰቡት መራመድን፣ ጽፈው ብቻ ሳይሆን ከተናገሩት በላይ ኖረው፣ ቃላቸውን በአርአያነት ተግብረው ያሳዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአረንጓዴ ዐሻራ ለመጣው ስኬት ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡

መሪ እና ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ተሰለፉ፤ አፈር ነክተው፣ ጭቃ ረግጠው ተስፋን ተከሉ፤እነርሱ ዝቅ ብለው ሀገርን ከፍ አደረጉ፤ኢትዮጵያውያን የመሪያችሁን ጥሪ ተቀብላችሁ፣ ከሠርቅ እስከ ሰርክ ተምማችሁ የአየር ሁኔታውን አሸንፋችሁ፣ ዕቅዳችሁን አሳካችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ዛፍ የሚተከለው ለትውልድ ነው፤ ስለዚህ ከጥላው ያረፉ፤ ከድርቅ የተረፉ፤ ከፍሬው የቀመሱ፤ ከልምላሜው የተቋደሱ ሁሉ ያመሰግኗችኋል ብለዋል፡፡

የዘንድሮውን የአንድ ጀንበር ሕልማችንን አሳክተናል፣ ለቀሪውም እንበርታ፣ በሁለመናዋ የበለጸገች አረንጓዴ ኢትዮጵያን እንገንባ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review