በሥራው ዓለም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስመዝግበዋል

You are currently viewing በሥራው ዓለም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስመዝግበዋል

AMN – ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በሥራው ዓለም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀንን (ሜይ ዴይ) ምክንያት በማድረግ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ዕለቱ የሠራተኛው መብት የሚታወጅበት ብቻ ሳይሆን የሥራ አካባቢ ምቹነት የሚረጋገጥበት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

የሠራተኛውን መብትና እኩልነት ለማስከበር በተደረገው ትግል በከተማዋ የመካከለኛ አመራር የሴቶች ተሳትፎ 43.3 በመቶ መድረሱን በስኬት ማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይም በሕግ አውጪውና በአስፈጻሚው የሴቶች ድርሻ 38 በመቶ፣ በዳኝነት ደግሞ 32 በመቶ መድረሱ የላብ አደሮች ቀን የሚዘክረውን የእኩልነት መርህ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቢሮው የሴት ሠራተኞችን የስራ ጫና ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰዱንም አብራርተዋል።

በዚህም እናቶች በሥነ-ልቦና ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በፌዴራልና በከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ውስጥ 713 የሕፃናት ማቆያዎች ተደራጅተው ከ11 ሺህ በላይ ሕፃናትን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ከዚህም ባለፈ ቀደም ሲል የነበረው የሦስት ወር የወሊድ ፈቃድ ወደ አራት ወር እንዲያድግ መደረጉና ለወንዶችም የሰባት ቀን የወሊድ ረዳት ፈቃድ መሰጠቱ በሥራው ዓለም የተመዘገበ ሌላኛው ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልም ልዩ ድጋፍና ቅድሚያ ዕድል መስጠትን መርህ ባደረገ መልኩ፣ በቅጥር ወቅት ሴቶች የሦስት ነጥብ ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በተጨማሪም በመኖሪያ ቤት አቅርቦት ረገድ የ30 በመቶ የቅድሚያ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉ በሠራተኛው ሕይወት ላይ ጉልህ ለውጥ ማምጣቱን ወ/ሮ ቆንጅት አስገንዝበዋል።

እነዚህ ስኬቶች ሠራተኛው በላቡና በጥበቡ ሀገርን ብሎም ዓለምን የሚቀይርበትን አቅም የሚያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህ በመዋቅራዊ ለውጥ የታጀበ ውጤት ለተተኪው ትውልድም ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቶች የሴት ተማሪዎች ውጤታማነት ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘንድሮውን የሠራተኞች ቀን ሲያከብር፣ ከመንግሥትና ከአሠሪ ማኅበራት ጋር በቅንጅት በመሥራት የሥራ ባህልን ለማሳደግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review