መንግስት የኢትዮጵያን ዘላቂ ህልውና እና አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው ሕብረ ብሔራዊነትንና አንድነትን፣ ሀገራዊና ገለልተኛ ተቋማትን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊነትን ያጣመረ ሚዛናዊ ሥርዓት ሲገነባ መሆኑን በጽኑ ያምናል። ልዩነትን እንደ ጸጋ በሚቆጥረው የ”መደመር” እሳቤ አማካኝነት፣ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ማንነትና መብት ያከበረ ጠንካራ የፌደራል ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ለአንድነት ቦታ ከማይሰጥ ሕብረ ብሔራዊነት እና ለሕብረ ብሔራዊነት ቦታ ከማይሰጥ አንድነት የወጣ፣ ሁለቱንም እሴቶች አጣጥሞ የያዘ ቀመር ነው። ይህ እሳቤ ኢትዮጵያ የየራሳቸው ማንነት ያላቸው ነገር ግን በታሪክና በባህል እጅግ የተሳሰሩ ህዝቦች ሀገር መሆኗን ዕውቅና የሚሰጥ ነው። ባለፉት የለውጥ ዓመታትም የሚያጋጩ ትርክቶችን ከማጉላት ይልቅ፣ የሚያቀራርቡና የሚያስተሳስሩ እውነታዎችን በማጉላት የእህታማማችነትና የወንድማማችነት ትስስርን ለማጠናከር ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል።
የመደመር መንግስት ካለፉት ታሪካዊ በደሎች ቁርሾን ከመፈልፈል ይልቅ፣ ስህተቶችን አርሞ ለወዳጅነት መጠናከር መጠቀምን ምርጫው አድርጓል። በዚህም መሠረት ዜጎች የሀገራቸውን ባህልና ማንነት ይበልጥ የሚያውቁባቸው የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የንግድ አማራጮች ተዘርግተዋል ። በተጨማሪም የሀገረ መንግሥቱን ፅናት ለማጠናከር ይረዱ ዘንድ እየተከናወኑ ያሉት ገለልተኛ የሆኑ የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ ተቋማትን የመገንባት የሪፎርም ሥራዎች በተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የቆየው በህዝቦቿ የጋራ አርበኝነት ሲሆን ፣ ሕብረ ብሔራዊነቱ የተጠበቀ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር አላማው ነው ። ይህንን ግብ ለማሳካትም የመደመር መንግስት በአስር ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ውስጥ እውነተኛ ሕብረ ብሔራዊ የፌደራል ሥርዓት ግንባታን እንደ ዋነኛ ምሰሶ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በቀጣይ የብዝኃ ቋንቋ ፖሊሲን ወደ ተግባር በማስገባት አካታችነትን ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ። የፌዴራል ሥርዓቱ ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ እንዲችልና የብሔሮች መብት የተከበረባት ሀገር እንድትገነባ ጥረት ይደረጋል ። ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት የግብርና ስኬቶችና የተገነቡት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች የመደመር መንግስት ለሀገሪቱ የሰነቀው ራዕይ በተጨባጭ ውጤት እየታጀበ መሆኑን ማሳያ ናቸው ።
“በኅብረት ሆነን እንበለጽጋለን፤ በልጽገንም በኅብረት እንኖራለን” በሚል መርህ ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከርና ለጋራ ብልጽግና ዕውን መሆን በአንድነት የሚቆሙበት ጊዜው አሁን ነው። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረትና አንድነት ወደ ላቀ ከፍታ መሸጋገሯ አይቀሬ ነው ፡፡