የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

You are currently viewing የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

AMN ሚያዝያ 28/2018

የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።

አቶ አደም ፋራህ ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በሶማሌ ክልል በሽንሌ ወረዳ የተገነባውን የ10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድና በሽንሌ ጠቅላላ ሆስፒታል የተገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

በወረዳው በባለሃብቶች የተገነቡና ወደ ማምረት የተሸጋገሩ የግራናይት ፋብሪካና ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በተጨማሪም በሽንሌ ወረዳ የመርማርሳ ከተማን ከድሬዳዋ ጋር የሚያስተሳስር የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታንም አስጀምረዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማረጋገጥ ተችሏል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በሶማሌ ክልል በፌደራል መንግስትና በክልሉ ጥምረት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ እመርታዊ ውጤቶችና ድሎች የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ የህዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ከማረጋገጥ ባሻገር በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካው ዘርፎች የመጡት ውጤቶች የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

በሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ የተመረቁትና ለህዝብ ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች የሀገራዊ ለውጡ እመርታዊ ጉዞ ማሳያ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የክልሉን ህዝብ ጥያቄዎች በመመለስ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስኬታማ ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በሽንሌ ወረዳ በተካሄደው የፕሮጀክቶች ምረቃና የጉብኝት መርሃግብር ላይ የክልሉና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review