AMN-ግንቦት 01/2018
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዲስ አበባ የምሽት ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።
በመዲናዋ የተገነቡት ፓርኮችና ማረፊያዎች ፣ በኮሪደር ልማቱ የተዘረጉት የመብራት መሰረተ ልማቶች አዲስ አበባን የብርሃን ፀዳል አላብሷታል።
መንገዶች ላይ የሚታዩት ባለቀለም መብራቶች ፣ በሕንፃዎቹ ላይ የሚንፀባረቁት ብርሃኖች እና በየቦታው የተሰሩት ፏፏቴዎች ለከተማዋ ዘመናዊና ማራኪ ገጽታ አጎናጽፈዋል።
ይህ መሰሉ የአዲስ አበባ ድምቀት ነዋሪዎችና ጎብኚዎች በምሽት ወጥተው እንዲዘዋወሩና የከተማዋን ውበት እንዲያጣጥሙ ጉጉትን የሚፈጥር ነው።
ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ሰማይ ለጭለማ እጅ ሲሰጥ አዲስ አበባ ሌላኛውን ውብ ገጽታዋን ከጉያዋ በሚፈልቁት ብርሃኖች ትገልጣለች።

ከቦሌ እስከ ካዛንቺስ፣ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያሉት ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና የባህል አዳራሾች ለእንግዶቻቸው አገልግሎት እየሰጡ የአዲስ አበባን ምሽት የበለጠ ያደምቃሉ።
ምሽቱ ለመዝናኛ ብቻ አይደለም ፣ ለብዙዎች የሥራና የኑሮ ማስቀጠያም ነው ።
የአዲስ አበባ ምሽት ያለው ሰላምና ደኅንነት ልዩ ያደርገዋል። ሰዎች በነፃነት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ፣ በየመንገዱ ዳር ሻይና ቡና እየጠጡ ሲጨዋወቱ ማየት የከተማዋ መገለጫ ነው።
የጥንታዊነትና የዘመናዊነት ስብጥሯ አዲስ አበባ ፣ የቀኑን ድካም የምታጥብ፣ አዳዲስ ተስፋዎችን የምታበቅልና በብርሃን የተንቆጠቆጠች ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማነትን እየተጎናጸፈች ትገኛለች።
አዲስ አበባ በምሽትም ጨለማ ውጧት የምታሸልብ ሳይሆን ፣ በደመቀ ፈገግታ ፣ የብርሃን ፀዳል ተጎናጽፋ ለነዋሪዎቿና ለንግዶቿ እፍይታንና ብርታትን ትለግሳለች።
ታደሠ ሽፈራው