ዜጎች የሚከበሩት የሀገር ፍቅርና ክብር ባላቸው ዜጎች ነው!

You are currently viewing ዜጎች የሚከበሩት የሀገር ፍቅርና ክብር ባላቸው ዜጎች ነው!

AMN – ግንቦት 10 / 2018 ዓ.ም

እንደ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ኤዥያ ባሉ የበለጸጉ ሀገራት የምገባ አገልግሎት፤ በተለይም በትምህርት ቤት፣ በሆስፒታል፣ በሥራ ቦታዎች እና ለአቅመ ደካማ ዜጎች የሚደረጉ የምገባ ፕሮግራሞች በጣም የዘመኑ፣ በህግ የተደገፉና ከሀገራቱ የጤና ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

የምገባ አገልግሎቱ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፤ ከጥብቅ የጥራት እና የጤና ቁጥጥር፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከሀገር በቀል ግብርና እና ለአቅመ ደካሞች ከሚደረግ የምገባ ድጋፍ ጋር ያገናኙታል፡፡

የዓለማችን ልዕለ-ኃያል የምትባለዋ አሜሪካ ለዜጎቿም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አሜሪካ ላቀኑ ግለሰቦች እንደ ቤተሰብ ገቢ መጠን ነፃ፣ በቅናሽ ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ ምሳ ታቀርባለች፡፡

በአሜሪካ ለተራበ ሰው ምግብ ከማቅረብ ባለፈ፣ በምግቡ ውስጥ ያለውን የስኳር፣ የጨው እና የስብ መጠን የመቀነስ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ጃፓን በትምህርት ቤት የምገባ አገልግሎት በዓለም ላይ በግንባር ቀደምትነት የምትነሳ ሲሆን፤ ለእነሱ ምገባ ረሃብን ማስታገሻ ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ትምህርት ነው።

ሕፃናት ምግባቸውን ራሳቸው ያቀርባሉ፣ ያጸዳሉ፣ ስለ ምግብ ንጥረ-ነገሮችና አመራረት ሂደትም በተግባር ይማራሉ፡፡ ምግቦቹ በሙሉ ትኩስ እና በአካባቢው ገበሬዎች የተመረቱ በመሆናቸው፤ የቀዘቀዘ ወይም በፋብሪካ የተቀነባበረ ምግብ ማቅረብ በሕግ አይፈቀድም።

ፊንላንድ ከመዋለ-ሕፃናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ሙሉ በሙሉ ነፃ የትምህርት ቤት ምገባ የምታቀርብ ሲሆን፤ የምግብ አገልግሎቱን የትምህርት ሥርዓቱ አንዱ አካል አድርጋዋለች፡፡

በርካታ የዓለም ሀገራት የምገባ አገልግሎትን ከትምህርት ጥራት፣ ከጤና መሻሻልና ከሀገር ውስጥ ምርታማነት ጋር አቀናጅተው የሚሰጡ ሲሆን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የትምህርት ቤት ምገባን በተግባር በመተርጎም ላይ ትገኛለች፡፡

ይህም በድህነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል፤ የቤተሰቦቻቸውንም የኑሮ ጫና በከፍተኛ ደረጃ አቃሏል፡፡

በተለይ አዲስ አበባ የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ፣ ጧሪና ጠያቂ የሌላቸው አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የሀገር ባለውለታዎች የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ቀዳሚዋ ከተማ ነች፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት፣ ልክ እንደሌሎቹ የልማት ሥራዎች ሁሉ በርካታ ትችቶችና አሉባልታዎች ቢሰነዘሩበትም፤ ከሀገር አልፎ አህጉር አቀፍ ተሞክሮ መሆን ችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክፍለ ከተሞች 29 የ”ተስፋ ብርሃን” የምገባ ማዕከላትን በመክፈት፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ፣ ጧሪና ጠያቂ የሌላቸው ዜጎች ዕለታዊ ጉርሳቸውን እንዲያገኙና የዜግነት ክብር እንዲሰማቸው በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያውያን ባህልም ሆነ በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮ መሠረት፤ ጤናማ ሆኖ መሥራት እየቻሉ መለመን አግባብነት የሌለው ተግባር ሲሆን፤ አቅመ ደካማ፣ አካል ጉዳተኛ፣ ጧሪና ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች መደገፍና መርዳት ደግሞ ለረጅም ዘመናት ከሕዝቡ ጋር የኖረ፣ እንደ መልካም ተግባር የሚታይ ትልቅ የአብሮነት እሴት ነው፡፡

ይህንኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት መሠረት በማድረግ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎች የምገባ አገልግሎትና መሰል ድጋፎችን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በመዲናዋ የሚኖሩ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህንን የመልካምነትና የአብሮነት ዓላማ በመደገፍ ወገኖቻቸውን በመርዳት የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ዜጎች የሚከበሩት የሀገር ፍቅርና ክብር ባላቸው ዜጎች እንደመሆኑ መጠን፤ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የምገባ አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሰማራት፣ በደግነትና በቅንነት ወገኖቻቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review