የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎበኙ

You are currently viewing የተለያዩ ሃገራት ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ጎበኙ

AMN ግንቦት 11/2018 ዓ.ም

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን፣ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ ፓርክን ጎብኝተዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ 14 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያለማና እያስተዳደረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከላት ኢንቨስትመንትን፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን፣ የኤክስፖርት እድገትን፣ተኪ ምርት ማምረትን፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት ታስበው የተገነቡ ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የአይሲቲ ፓርክን ጨምሮ በእነዚህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ300 በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ጉብኝቱ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ለሚገኙ ባለሀብቶች የሚደረገውን ድጋፍና አጋርነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆኑንና በተለይም ልዩ የኢንኮኖሚ ዞኖች የተለያዩ ሀገራት ባለሀብቶችና አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያነሳሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዲፕሎማቶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አልምቶ ከሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በተጨማሪ በግል ባለሃብቶች የለሙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸዉን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review