AMN – ግንቦት 12/2018 ዓ.ም
ዛሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሚራመድ ማንኛውም ሰው የሚመለከተው ነገር ቢኖር የከተማዋን መልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን፣ በአህጉሪቱ ላይ እየተቀረጸ ያለውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ለዓመታት በበዛ መጨናነቅ እና ባልተቀናጀ መሰረተ ልማት ስትታወቅ የነበረችው አዲስ አበባ፣ ዛሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሷን አድሳ ምቾት፣ ውበት እና ዘመናዊነት መላበስ ችላለች።
ይህ አስደናቂ ሽግግር እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ከዓለም አቀፍ ከተሞች የተወሰዱ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዋህዶ በተግባር የመተርጎም ውጤት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህንን ፈጣንና ስር ነቀል ለውጥ አስመልክተው ሲናገሩ፣ የከተማዋ እድገት ትልቅ ዓላማን ያነገበ መሆኑን በግልጽ አመላክተዋል።
ከንቲባዋ እንዳሉት፣ “አዲስ አበባን ስንገነባ ስሟ እንደሚመሰክረው ሁልጊዜም አዲስ እና ውብ፣ ለነዋሪዎቿ የምትመች፣ ለጎብኚዎቿም ማራኪ እንድትሆን በማሰብ ነው።
ከዓለም አቀፍ መዲናዎች የቀሰምናቸውን ምርጥ ልምዶች ከራሳችን አቅም፣ ባህልና እሴት ጋር በማጣመር የጀመርናቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከተማዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዘመን ችለዋል።
ይህ ስኬት ደግሞ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚገባቸውን የኑሮ ደረጃ ከመፍጠር ባለፈ፣ ለተቀሩት የፈጣን እድገት ባለቤት ለሆኑ የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ ተሞክሮ እና ተግባራዊ ማሳያ መሆን ችሏል ይላሉ፡፡

ይህንን የለውጥ ማዕበል በግንባር ቀደምትነት ከሚመሩት ፕሮጀክቶች መካከል በቅርቡ የተከናወነው ሰፊው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
እንደ ፓሪስ እና ሴኡል ካሉ የዓለም ታዋቂ ከተሞች በተወሰደው የልማት እቅድ መሰረት፣ የከተማዋ መንገዶች ለተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን ለእግረኞች ምቹ የሆኑ ሰፋፊ የእግር መንገዶችን፣ የብስክሌት መስመሮችን እና አረንጓዴ መናፈሻዎችን አካተው ተገንብተዋል።
ይህም ነዋሪው በነጻነት የሚንቀሳቀስባት እና ማህበራዊ ህይወቱን የሚያድስባት ከተማ እንድትፈጠር ከማድረግ ባሻገር የአለም የስበት ማዕከል እንድትሆን አስችሏል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በከተማዋ የተዘረጉት እንደ እንጦጦ፣ ሸገር እና ወዳጅነት ያሉ ታላላቅ ፓርኮች አዲስ አበባን በአረንጓዴ ልማት ረገድ የሲንጋፖርን ፈጠራ እንድትጋራ አድርገዋታል።
ከተማዋ በህንፃዎችና በኮንክሪት ብቻ ሳትታጠር፣ ተፈጥሮና ዘመናዊነትን ጎን ለጎን የሚሄዱበት ስነ-ምህዳርም ተፈጥሯል።
ከተማዋን ወደ ስማርት ከተማነት ያሻገራት ትልቁ እርምጃ የዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋትም ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተደጋጋሚ እንደሚያስረዱት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የከተማዋን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ግልጽ እና ከሙስና የጠራ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የመንግስት አገልግሎቶችን በድረ-ገጽ ማቅረብ፣ የትራፊክ ቁጥጥርን በካሜራዎች ማዘመን እና እንደ ቴሌብር ያሉ የዲጂታል ክፍያ ስርዓቶችን ማጠናከር ከተማዋን ከተራቀቁት የኤዥያ መዲናዎች ጋር እኩል ተጓዥ አድርጓታል።

አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የደረሰችበት የላቀ ደረጃ የሚያሳየው ዓለም አቀፍ እውቀትን ከአገር ውስጥ ቁርጠኝነት ጋር አጣምሮ መነሳት ያለውን ጉልበት ነው።
መዲናችን የዓለምን ስልጣኔ እንዲሁ በጭፍን አልገለበጠችም፤ይልቁንም የራሷን መለያ ማንነት ጠብቃ፣ የነዋሪዎቿን የዘመናት የልማት ጥያቄ በመመለስ ላይ ትገኛለች።
ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ድል፣ “የአፍሪካ ዋና ከተማ” የተሰኘውን ስሟን በተግባር በማደስ፣ ወደፊት እንድትራመድ አዲስ የብርሃን ፋና ሆኖ ያገለግላል።
ከተማዋ ዛሬም እንደትላንቱ ሰርክ አዲስ ለመሆን ከንቲባ አዳነች አበቤን ጨምሮ የተለያዪ የመዲናዋ ስራ ሃላፊዎቸ በአዘርባጃን ባኩ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በሚካኤል ህሩይ