የምርጫ ዕለት ድምፃችንን ለምንፈልገው አካል በመስጠት መብታችንን በንቃት ልንጠቀምበት ይገባል- ሲቪል ማሕበራት

You are currently viewing የምርጫ ዕለት ድምፃችንን ለምንፈልገው አካል በመስጠት መብታችንን በንቃት ልንጠቀምበት ይገባል- ሲቪል ማሕበራት

AMN – ግንቦት 12/ 2018 ዓ.ም

ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጮች ካርድ በመውሰድ ብቻ ሳይወሰኑ በዕለቱ በንቃት ወጥተው ድምፅ በመስጠት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ እንደሚገባ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አሳስበዋል።

ማህበራቱ ምርጫን ቀለል አድርጎ ከመመልከት ወጥቶ እያንዳንዱ ዜጋ በቀጣይ አምስት ዓመታት ያስተዳድረኛል፣ ይጠቅመኛል የሚለውን አካል በነጻነትና በንቃት መምረጥ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትን ስኬታማና ሰላማዊ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅትና ቅስቀሳ እያደረጉ መሆኑን ነው የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶቹ ያስታወቁት።

የምርጫ ቦርድ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የማርያምወርቅ ከበደ፤ ማህበራቱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲቀሰቅሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን ተከትሎ መራጮች የያዙትን ካርድ በመጠቀም የሚፈልጉትን አካል እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በምርጫው እለትና ከምርጫው በኋላ ያለውን ሂደት የሚታዘቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ታዛቢዎችን ለማሰልጠን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር ተወካይ ስርጉት ይመር፤ የሴት አካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ላለፉት 4 ወራት ግንዛቤ ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይ ቀናትም በምርጫው እለት ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ጥንቃቄዎችና ስላላቸው መብቶች የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ሁሉም የመረጠው አካል ወደ ስልጣን ላይመጣ ይችላል፣ ምርጫ በመሆኑ አብላጫ ድምጽ ያገኘውን አካል ተቀብሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንዲመራ እራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴንም የተለያዩ ማህበራት ወጥታችሁ ምረጡ፣ ካርድ ውሰዱ በማለት ሰፊ የመራጮች ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበረሰቡ ካልተረጋገጡና አስቀድመው ከሚወጡ መረጃዎች እራሱን መጠበቅ እንዳለበትም የማርያምወርቅ ከበደ አሳስበዋል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመላክተው 50 ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ ለዚህ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቧል።

ምዝገባ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ሲቪል ማሕበራቱ በምርጫው እለት ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በንቃት ወጥተው ድምፅ እንዲሰጡና የምርጫውን ውጤት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review