ሩሲያና ቻይና በሉዓላዊ ሃገራት ላይ የሚፈጸሙ የውስጥ ጣልቃገብነቶችንና ጥቃቶችን አወገዙ

You are currently viewing ሩሲያና ቻይና በሉዓላዊ ሃገራት ላይ የሚፈጸሙ የውስጥ ጣልቃገብነቶችንና ጥቃቶችን አወገዙ

AMN ግንቦት 12/2018 ዓ.ም

ሩሲያና ቻይና በሉዓላዊ ሃገራት ላይ የሚፈጸሙ ወታደራዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሀገር መሪዎችን መግደልን ፣ የሃገራትን የውስጥ ፖለቲካ ማወክን እና የመንግሥት ለውጥ መነሳሳትን አወገዙ፡፡

የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቻይና ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከቻይናዉ አቻቸዉ ሺ ጂንፒንግ ጋር በንግድ፣ በቴክኖሎጂ እና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመምከር የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በኃይል ዘርፍ ያለውን አጠቃላይ አጋርነት ለማጠናከር እና በነዳጅ፣ ጋዝ እና ከሰል ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡

ሩሲያና ቻይና በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ለመገንባት ያላቸውን ዕቅድ እንደገና ያረጋገጡ ሲሆን ስምምነቱ ለዓመታት ተግባራዊ ሳይሆን መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በዩክሬንና ኢራን ጦርነት ዙሪያ የመከሩ ሲሆን ጦርነቶቹ መቆም እንዳለባቸዉ አስገንዝገዋል፡፡ ቤጂንግ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጉዳይ በተለያዩ ጊዜአት ገለልተኛ አቋም መያዟ ይታወሳል፡፡

የኢራንን ጦርነት በተመለከተም ቤጂንግ የነዳጅ ክምችት ቢኖራትም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱ የነዳጅ እጥረቱን አራዝሞባታል፡፡

ሃገሮች በአንድ ወገን ብቻ በዓለም ንግድና የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ጣልቃ መግባት እንዲያቆሙ ቻይናና ሩሲያ ጠይቀዋል፡፡

የሆርሙዝን ጉዳይ በይፋ ባይጠቅሱም አንዳንድ ሃገሮች፣ በአንድ ወገን ብቻ የሚወስዱት እርምጃ ዓለም አቀፍ የባሕር መጓጓዣን እና የንግድ ሰንሰለቶችን አደጋ ውስጥ ስለመጣሉ አጀንዳ አድርገዉ ተነጋግረዉበታል፡፡

የወደብ እና የባሕር መሠረተ ልማት ትብብር በገበያና በንግድ መርሆዎች ላይ መመስረት አለበት ብለዋል ሁለቱ ሃገራት፡፡

ፑቲን እና ሺ ጂንፒንግ ተንኮልን ያዘሉና በሌሎች አገሮች ላይ የሚፈጸሙ ወታደራዊ ጥቃቶች፣ ድርድርን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለጥቃት ማዘጋጀት፣ የሀገር መሪዎችን መግደል፣ የሃገራትን የውስጥ ፖለቲካ ማወክ እና የመንግሥት ለውጥ ማስነሳትን ማዉገዛቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እነዚህ ድርጊቶች የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርንና ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ ይጥሳሉ፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተውን የዓለም ሥርዓትም ያበላሻሉ ብለዋል መሪዎቹ፡፡

የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የቻይናዉ አቻቸዉ ሺ ጂንፒንግ በዓለም ሥርዓት ላይ የሚነሱ ስጋቶችን በመከላከል፣ እራሳቸውን የአዲስ ዓለም ሥርዓት አስተዳዳሪዎች እንደሆኑ ለማቅረብ እየሞከሩ መሆናቸዉን አንዳንድ ተንታኞች ተናግረዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review