AMN- ግንቦት 10/ 2018 ዓ.ም
የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያስገነባቸውን 295 የተቀናጀ የከተማ ግብርና ሼዶችን አስመርቋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንደገለፁት መንግስት ወጣቶችን ከስራ አጥነት በማላቀቅ ወደ አምራችነትና ራስን መቻል ለማሸጋገር በተቀናጀ መንገድ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የቢሮ ሀላፊው የከተማ ግብርና ዘርፍ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የኑሮ ውድነትን በመቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍፁም ሀይሌ በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በመግለፅ፣ እስካሁን 34 ሺህ 991 ዜጎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በንግድና በከተማ ግብርና ዘርፎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ከተማ ግብርና በአዲስ አበባ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና ወጣቶችን ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ዋና አማራጭ መሆኑን አንስተው፣ እንደ የካ ያሉ ክፍለ ከተሞች እያሳዩ ያሉት ተግባራዊ ልምዶች ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ እንደተገለፀው የተቀናጀው የከተማ ግብርና ሼድ ወጣቶችን ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲፈጥሩ ከማገዝ ባለፈ፣ የከተማውን የምግብ አቅርቦት በማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በንጉሱ በቃሉ