AMN – ግንቦት 15/2018 ዓ.ም

ማንኛውም እርግዝና በሚፈጠርበት ጊዜ ጽንሱ ማደግና መተከል ያለበት በማህፀን ግድግዳ ውስጥ ቢሆንም ፣ አልፎ አልፎ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ጽንሱ ከማህፀን ውጭ በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ዓይነቱ ክስተት ከማህፀን ውጭ የሚከሰት እርግዝና (Ectopic Pregnancy) ይባላል።
ስለ ችግሩ አሳሳቢነት፣ መንስኤዎችና ምልክቶች በአበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶክተር አህመድ ባቡ ለኤ ኤም ኤን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

ዶክተር አህመድ እንደገለጹት፣ በአብዛኛው ከማህፀን ውጭ የሚከሰት እርግዝና የሚያጋጥመው በማህፀን ቱቦ ላይ ነው። ሆኖም ግን አልፎ አልፎ ከማህፀን ቱቦ ውጭ በዘር ፍሬ ላይ፣ በሆድ ዕቃ ውስጥ፣ በማህፀን በር ላይ በጣም አልፎ አልፎ ደግሞ ቀደም ሲል በቀዶ ጥገና የወለዱ ሴቶች ላይ ጠባሳው ባለበት ቦታ ላይ ሊከሰት ይችላል።
የማህፀንና አካባቢው ኢንፌክሽን ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው በአባለዘር በሽታዎችና ከእነሱ ጋር ተያይዘው በሚመጡ ውስብስብ ችግሮች ሳቢያ እንደሆነ ነው ዶክተር አህመድ የጠቀሱት።
አንዲት ሴት የወር አበባዋ ከቀረ በኋላ የታችኛው ሆድ አካባቢ ወይም ከእምብርት በታች ከባድ ህመም መሰማት፣ የተወሰነ መጠን ያለው የደም መፍሰስ ማጋጠም ምልክቶች በአንድ ላይ ከተከሰቱ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡
እነዚህ ምልክቶች የፅንስ ውርጃ ምልክቶች ሊሆኑ ቢችሉም፣ ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝናም ሊሆን ስለሚችል ማንኛዋም ሴት እነዚህን ምልክቶች ካየች በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚጠበቅባት የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪሙ አሳስበዋል።

የሕክምናው ዓይነት የሚወሰነው ችግሩ በተደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ ተመስርቶ ነው ያሉት የሕክምና ባለሞያው ፣ ይህም ፅንሱ ሳይፈነዳ በጊዜ እና ቀድሞ ከተገኘ በመድኃኒት ብቻ ማከም ይቻላል ብለዋል፡፡
ፅንሱ በቱቦው ውስጥ አድጎ ከፈነዳ በኋላ ግን እናትየው ላይ ከባድ የውስጥ ደም መፍሰስና ለሕይወት አስጊ የሆነ አደጋ ስለሚያስከትል የግድ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እርግዝና ሁልጊዜ ማህፀን ውስጥ ብቻ ላይፈጠር ይችላል የሚሉት የሕክምና ባለሞያው ከማሕጸን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና አልፎ አልፎ እስከ 9 ወር ድረስ የሚዘልቅበት በጣም ጥቂት አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ በአብዛኛው ግን እዚያ ሳይደርስ ስለሚፈነዳ በእናትየው ላይ ከፍተኛ አደጋ ያመጣል ብለዋል።
ስለዚህ የመውለጃ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች በሙሉ የወር አበባ ሲቀርና የሆድ ህመም ሲኖር ወደ ጤና ተቋም በመሄድ እርግዝና መኖሩንና ካለም የት ቦታ ላይ እንዳለ በጊዜ ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር አህመድ ባቡ መክረዋል።
ለአባለዘር በሽታዎች አጋላጭ የሆኑ ባህሪያትን በመከላከል ይህንን ችግር መቀነስ እንደሚቻልም ነው የጠቀሱት።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ