የበዓላቱ ተጨማሪ ድምቀት

You are currently viewing የበዓላቱ ተጨማሪ ድምቀት

  • የኮሪደር ልማቱ የፈጠረው ውብና ምቹ ገፅታ በከተማዋ የሚከናወኑ ኃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን አይረሴ ትዝታ እንደሚያጎላ ተገልጿል

አሁን አዲስ አበባ እንደ ፅጌሬዳ ፈክታለች፤ አዲስ ውበትን፣ ማራኪ ገፅታን ተላብሳለች፡፡ ከስሟና ከታሪኳም ጋር ታርቃለች፡፡ ለበርካቶችም የዐይን ማረፊያ ሆናለች፡፡ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በብቃት ማስተናገድም ጀምራለች፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ኃይማኖታዊ እና የህዝብ በዓላትን ከአዲስ አበባ ውብ ጎዳናዎች ጋር መመልከት ልብን ያሞቃል። አዲስ አበባን እንደ አዲስ በወለደው ፅዱ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ ምቹና ሰፋፊ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶች ከሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎቿ ጋር ተዳምረው ከተማዋን እንደ ሙሽራ አስውበዋታል፡፡

በከተማዋ የተገነቡት የአውቶብስና የታክሲ ተርሚናሎች፣ የምድር ውስጥ ፓርኪንግ፣ የታክሲ ማውረጃና መጫኛ ቦታዎች፣ የመሮጫ ትራኮች፣ የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች እንዲሁም ዘመናዊ የእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች የትራፊክ ፍሰቱን ጤናማ ያደረጉና የትራንስፖርት አገልግሎትን ያሻሻሉ ናቸው፡፡ በኮሪደር ልማቱ የተሰሩት መሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ነዋሪዎች ለበዓላቸው ድምቀት፣ ለድካማቸው እረፍት እና ለገቢያቸውም ምክንያት ሆነዋል፡፡

በእርግጥም “ስለ አዲስ አበባ አስገራሚ ለውጥ ለመናገር ምስክር አያሻም፤ ምክንያቱም ከተማዋ እንደስሟ አበባ እየሆነች ስለመምጣቷ የተመለከታት ሁሉ ምስክር ነው” ይላሉ የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አህመድ ከማል፡፡ በመዲናዋ ከ35 ዓመታት በላይ እንደኖሩ የነገሩን አቶ አህመድ እንደሚሉት ከተማዋ ቀደም ባሉት ዘመናት ነግዶ ለማትረፊያ እንጂ ያን ያህል ለመኖሪያ ምቹ አልነበረችም፡፡

ምክንያቱም ንፅህናቸውን ያልጠበቁ መንገዶች እና መንደሮች በብዛት ከመኖራቸውም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ክረምት በመጣ ቁጥር አሊያም ሙቀቱ በሚያይልባቸው ወቅቶች ወረርሽኞች ጭምር ይከሰቱ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በከተማዋ እየተከናወነ ባለው ልማት እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ከተማዋ ለንግድ ብቻ ሳይሆን ለመኖሪያም የምትመረጥ፣ ጎዳናዎቿ የሚያምሩ ውብ ከተማ ሆናለች፡፡ በዚህ ላይ እንደ አረፋን የመሳሰሉ በዓላትን ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ሲያከብር ከህብረ ቀለማቱ ውበት ጋር የተዳመረ ገፅታዋ ጎልቶ ሲወጣ እጅጉን ታምራለች ይላሉ አቶ አህመድ፡፡

ወይዘሮ ፎዚያ አሕመድ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ውበት ነግቶ በጠባ ቁጥር አዲስ እየሆነ ነው፡፡ ከመዋባቸው የተነሳ አንዳንድ የማውቃቸው ስፍራዎች ጭምር ግር እያሉኝ መጥተዋል ይላሉ፡፡ ይህን መሰል ለውጥ ከእኛ ባሻገር ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን ትልቅ ሀብት እንደማስቀመጥ ነው፡፡ በተለይም እንደ አረፋን እና ኢድ አል ፈጥርን የመሳሰሉ ኃይማኖታዊም የሆኑ ሌሎች በዓላትን በአደባባይ ወጥተው ሲያከብሩ የከተማዋ አሁናዊ ገፅታ ደስታቸውን አይረሴ እንደሚያደርገውም አጫውተውናል፡፡

የፎክሎር ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በዛ ያሉ ቢሆኑም በተለይ እንደ አረፋ፣ ኢድ አል ፈጥር፣ ጥምቀት፣ መስቀል፣ ኢሬቻ እና ሌሎቹም ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች በድምቀት የሚከበሩና የማህበረሰቡን እሴት በጉልህ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡

በእነዚህ በዓላት የሚታደሙ ኢትዮጵያውያን በተለይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ሲታዩ ህብረ ብሔራዊነት ነፍስ ዘርቶ የሚደምቅበት፣ የማህበረሰቡ የተለያዩ ውብ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች፣ ባህላዊ አልባሳት እና ቀልብን በሚገዙ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በኮሪደር ልማቱ ውብ ገፅታን በተላበሱት የመዲናዋ አደባባዮች የኢትዮጵያውያንን መልክና ልክ አጉልተው ሲያሳዩ በርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡

አዲስ አበባ እንደ አዲስ ውበቷ እየፈካ፣ ጎዳናዎቿ እንደ ፅጌሬዳ አበባ የሚያሳሱ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ታዲያ በእነዚህ ውብ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ እንደ አረፋ እና ኢድ አል ፈጥርን የመሳሰሉ ኃይማኖታዊና የህዝብ በዓላት ሲከበሩ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን ለበዓላቱ  ደግሞ ድርብ ድምቀትን ይሰጣሉ፡፡

ኃይማኖታዊም ሆነ የህዝብ በዓላት ህዝቡ በክት ልብሱ ደምቆ፣ መልካም መንፈስን ታጥቆ እና ከቤቱ ወጥቶ የሚያከብራቸው በዓላት በመሆናቸው በህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ናቸው፡፡ ታዲያ የበዓላቱና የአደባባዮቹ ድምቀት አብሮ ሲደመር ለከተማዋ ትልቅ ፍካትን ይፈጥራሉ፡፡ የማህበረሰቡም መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱም ዕድል ይሆናሉ  ይላሉ፣ የፎክሎር ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ፡፡

የኢትዮጵያውያን ውብ ባህላዊ እሴቶች እንዲህ ደምቀው በአደባባይ ሲታዩ፣ ለሌላው ዓለም የህዝቡን መልካም ገፅታ እንዲሁም የሀገርን ሁለንተናዊ ከፍታ ያሳያሉ፡፡ እየለማ ያለው ግዑዝ የሆነው ቦታ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡም ነባር እሴት በመሆኑ  በማህበረሰባዊ፣ በኢኮኖሚያዊም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሰዎች ልባቸውንም፣ ልብሳቸውንም አፅድተው በህብረት የሚያከብሯቸው በመሆኑ ንፁህ ስፍራዎችም ያስፈልጓቸዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ያስገኘው አንዱ በረከትም ለእነዚህ በዓላት ምቹ ማክበሪያ ቦታዎችን ነው፡፡ በመሆኑም የማህበረሰቡን ስጋና ነፍስ ለማስደሰት ትልቅ አቅምን ፈጥሯል። ይህም ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ለበዓላቱም አይረሴ ድምቀት ነውም ብለዋል፡

አክለውም፣ ማህበረሰቡ በእነዚህ ስፍራዎች የአደባባይ በዓላትን ያለምንም መጨናነቅ በፍፁም ደስታና ውበት ሲያከብር ሀገራዊ ኩራት እንዲሰማው ይሆናል፡፡ የተሰራው ልማት ለእርሱ እንደሆነም በሚገባ እንዲረዳው፣ ልማቱንም እሴቱንም እንዲጠብቅና እንዲያከብር ያነሳሱታል፡፡

በርካታ ሀገራት ጎዳናዎችን፣ አደባባዮችን እና መናፈሻዎችን ወደ ደማቅ የበዓል ማክበሪያ ማዕከልነት በመቀየር ባህሎቻቸውን እያሳደጉ እና እያበለጸጉ ነው ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) The Impact of Heritage Conservation on Cultural Development በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ መስከረም 26 2025 ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡

ለአብነትም ጃፓን፣ ስፔን እና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ህዝባዊ በዓላቶቻቸው ከፍ ብለው እና ደምቀው እንዲታዩ ጎዳናዎቻቸውን እና አደባባዮቻቸውን በማስዋብ ዓለም አቀፍ ትኩረትን መሳብ ችለዋል፡፡

ጃፓን ቶኪዮን በመሳሰሉ ከተሞቿ በየዓመቱ የሚከበሩት በዓላቶቿን በሰፋፊ አደባባዮች፣ መንገዶችና ፓርኮች ላይ የበዓሉ ታዳሚዎች በአበቦች፣ በዛፎች እና በውብ ፏፏቶዎች  ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ ታደርጋለች፡፡ ይህም በመላው ዓለም በዓላቱ ትኩረት እንዲስቡ ምክንያት እንደሆነም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

በዓለም ዙሪያ የባህል እና የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች በየዓመቱ ከ2 ነጥብ 25 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ያመነጫሉ። ይህም ወደ 30 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድልም ይፈጥራል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ የባህል ቱሪዝም ከዓለም ጉዞዎች ውስጥ 40 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማቱ የፈጠረው ውብና ምቹ ገፅታ በየዓመቱ ለሚከናወኑ ኃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት አይረሴ ትዝታን እና ተናፋቂ ድባብን ከመፍጠራቸው ባሻገር ከተማዋ በባህል ቱሪዝም ዘርፍም የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድልም የሚፈጥር ነው፡፡

የከተማ ልማት ባለሙያው እና አማካሪ ኢንጂኒየር በሱፈቃድ አየለ እንደሚሉት ስለ ዘመናዊ ከተማ ልማት ስናስብ ስለ መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን ስለ የማህበረሰቡን እሴት፣ ወግና ልማድ ታሳቢ ማድረግን፣ ማህበራዊ ግንኙነትን ማጠናከርና የመሳሰሉትንም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው የአዲስ አበባ አሁናዊ ልማት ምስክር ነው፡፡

ለአብነትም ለተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን ለእግረኞችም ተስማሚ የሆኑ መንገዶችን፣ መብራቶችን እና አረንጓዴ ቦታዎችን ከሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር አዋህዶ መስራት ከዘመናዊ የከተሜነት እሳቤ ባሻገርም ምን ያህል በማህበረሰቡ ዘንድ እርካታን እንደሚፈጥር እና ማህበራዊ ትስስርን እንደሚያጎለብት በኮሪደር ልማቱ መመልከት ችለናል፡፡

በከተማዋ የተሰሩ መናፈሻዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ፕላዛዎች፣ የእግረኛ መንገዶች ከመዝናኛነት ባለፈ ለነዋሪዎቹ የገቢ ምንጭ እያስገኙ ነው፡፡ ለአብነትም በፎቶ ማንሳት ሙያ የተሰማሩ ወጣቶችን መጥቀስ እንችላለን፡፡

በ4 ኪሎ ፕላዛ ላይ ፎቶ ግራፍ በማንሳት የሚተዳደረው ወጣት መኮንን ሲሳይ የኮሪደር ልማቱ ለእሱና ለጓደኞቹ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞለት የመጣ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በ500 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጥሮ ፎቶ ግራፍ የማንሳት ስራውን የጀመረው ወጣት መኮንን አሁን በ100 ሺህ ብር ዘመናዊ ካሜራ በመግዛት በ4 ኪሎ ፕላዛ አካባቢ ፎቶ ግራፍ በማንሳት ህይወቱን እየመራ ይገኛል፡፡

ከዓመት በፊት ሸራተን ሆቴል አካባቢ ፎቶ ሲያነሳ እንደነበር ያጫወተን ወጣት መኮንን ኮሪደር ልማቱ በፈጠረለት ተጨማሪ አቅም አሁን ከ4 ኪሎ ፕላዛ እስከ ፒያሳ ድረስ ባለው መንገድ  ነዋሪዎችን ፎቶ በማንሳት ገቢ እያገኘ ነው፡፡

እሱ እና ጓደኞቹ በአዲስ አበባ ፓርኮች አስተዳደር ስምንት ወጣቶች በመሆን በ“ሙሴ እና ኦሊያድ ጓደኞቻቸው ፎቶ አንሺ ማህበር” ተደራጅተው ፎቶ ግራፍ እያነሱ ሕይወታቸውን በተሻለ መልኩ እየመሩ ስለመሆኑም አጫውተውናል፡፡

በእርግጥም የኮሪደር ልማቱ ያስገኛቸው በረከቶች ነዋሪዎች ደስታቸውን የሚያጣጥሙባቸው፣ ማህበራዊ ሕይወታቸውን የሚያጎለብቱባቸው እና ኢኮኖሚያቸውን   ከፍ  የሚያደርጉባቸው የለውጥ መስኮት መሆናቸውን በርካቶች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review