የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባከናወናቸው ሰፊ የልማትና የማሻሻያ ሥራዎች፣ በትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የተማሪዎች ቁጥር ከ829ሺህ 158 ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በማሳደግ ትምህርት የማይገቡ ሕፃናት እንዳይኖሩ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በ6ተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከ50 በላይ ያመጡ ተማሪዎች ከ80ነጥብ 2 በመቶ ወደ 97 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ፣ በተከታታይ በተከናወኑ የጥራት ቁጥጥር ተግባራትም በ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ከተማ አቀፍና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ መሻሻል ተመዝግቧል ብለዋል።

ትምህርት ቤቶችን ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ምቹ ለማድረግ የልዩ ፍላጎት ማዕከላትን ቁጥር ወደ 124 ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፣ ለአይነ ስውራን ተማሪዎች የብሬል መጽሐፍ ሕትመት በማከናወን በወቅቱ ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለ36 የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት ቤቶች እንደ ሄድፎን ፣ ነጭ በትር ፣ የድምፅ ሰዓትና የድምፅ ካልኩሌተር ያሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችንና የአካል ድጋፍ ግብዓቶችን ማሟላት መቻሉን አብራርተዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review