AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማን የአየር ንብረት ተጋላጭነት ለመቀነስና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠበቅ የተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት እጅግ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
6 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ 16 ኮሪደሮችና 8 ወንዞችን ያካተተው ይህ ሰፊ የአረንጓዴ ልማት ፣ የከተማዋን ስነ-ምህዳር ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ መሆኑን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ባቀረቡት ዓመታዊ አፈጻጸም ሪፖርት አብራርተዋል፡፡

59 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ሰፊ የልማት ስራ የተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከተማዋ 2 ሺህ ሄክታር አዲስ አረንጓዴ ሽፋን እንድታገኝ መደረጉንም ገልጸዋል።
የአካባቢን የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅና የውሃ ሀብትን ለማልማትም 24 የውሃ ግድቦች ፣ 66 ቼክዳሞች እንዲሁም 3 ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሀይቆች ተገንብተዋል ብለዋል።
ነዋሪዎችና ጎብኚዎች በተፈጥሮ እየተደሰቱ እንዲንሸራሸሩም 51 ያህል ውብ የእግረኛ ድልድዮችና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶች በወንዝ ዳርቻዎች ላይ መገንባታቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ታደሠ ሽፈራው