ነብዩ መሐመድ የሚወዷቸው ቀለማት

You are currently viewing ነብዩ መሐመድ የሚወዷቸው ቀለማት

ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ መጀመሪያ የምናስተውለው ምንድን ነው? የሰማዩን ሰማያዊነት፣ የቅጠላ ቅጠሎችን አረንጓዴነት ወይንስ የፀሐይዋን ወርቃማ ብርሃን? በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ቀለማትን እንደ ተራ የተፈጥሮ ክስተት ብቻ ልናያቸው እንችላለን። ነገር ግን፣ ቀለማት ለአይን የሚታዩ ውበቶች ብቻ አይደሉም፤ እነሱ ከሰው ልጅ ሥነ-ልቦና፣ ታሪክ፣ ባህል እና መንፈሳዊነት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ የዓለማችን ህያው ቋንቋዎች ናቸው።

የሰው ልጅ በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቀለማትን እንደ መገናኛ፣ መግለጫ እና መለያ መሳሪያ ሲጠቀምባቸው ኖሯል። ምክንያቱም ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን ጥልቅ ስሜት፣ ረቂቅ እምነት እና የጋራ ማንነት በአንድ ቀለም ውስጥ አምቆ ማሳየት ይቻላልና። ቀለማት የድንበር አጥርን ጥሰው፣ የቋንቋ ልዩነትን አሸንፈው በቀጥታ ከሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና ጋር ይነጋገራሉ። የሰው ልጅም ከፈጣሪው እና ከማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት ለመግለጽ ቀለማትን እንደ ትልቅ ድልድይ ይጠቀማል። በእምነት ተቋማት ውስጥ እያንዳንዱ ቀለም ዝም ብሎ የሚመረጥ ሳይሆን፣ ጥልቅ መለኮታዊ እና ምስጢራዊ ትርጉም ያዘለ ነው። ይህ ጽሑፍ የአረፋ በዓልን ምክንያት በማድረግ  ነብዩ መሐመድ የሚወዷቸው ቀለማት እና ትርጓሜያቸውን እንዲሁም በእስልምና እምነት ውስጥ ያላቸውን ስፍራ  ይተነትናል።

ቀለማት እና እስልምና

ቀለማት በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ስሜትን የመግለጽ፣ ውበትን የመፍጠርና መልዕክትን የማስተላለፍ ትልቅ አቅም አላቸው። በእስልምና አስተምህሮ እና ታሪክ ውስጥ ደግሞ ቀለማት ከተራ ውበት ማድመቂያነት አልፈው ጥልቅ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ሥነ-ልቦናዊ ትርጉም ይይዛሉ። በቅዱስ ቁርዓን እና በነቢዩ መሐመድ ሐዲሶች (ትምህርቶች) ውስጥ ለተለያዩ ቀለማት የተሰጡት ቦታዎች፣ በእስልምና ጥበብ (Art)፣ ሥነ-ህንጻ (Architecture) እና አልባሳት ላይ የጎላ አሻራ አሳርፈዋል።

ሁሉንም ቀለማት አቅፎ የያዘውና የብርሃን ነጸብራቅ የሆነው ነጭ ቀለም እና ሁሉንም ቀለማት በውስጡ የሚሰበስበው ጥቁር ቀለም በእስልምና እምነት  ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው። አረንጓዴ ቀለም በእስልምና እምነት ውስጥ እጅግ የላቀና የተቀደሰ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በተጨማሪም ሰማያዊ ቀለም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ታሪክና ስልጣኔ ውስጥ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የጥልቅ እውቀትና የመለኮታዊ ውበት መገለጫ፣ የሰማይን ስፋትና ጥልቀት የሚያስታውስ፣ አማኞች ወደ ላይ ሲመለከቱ የፈጣሪን ስፋትና ወሰን የለሽ ኃይል እንዲያስቡ የሚያደርግ መንፈሳዊ ድልድይ ተደርጎ ይታያል።

ነጭ

በእስልምና አስተምህሮ እና ባህል ውስጥ ነጭ ቀለም እጅግ የላቀ፣ንጹህ እና የተከበረ ቦታ አለው። በዚህም ነብዩ መሐመድ በንግግራቸውም ሆነ በተግባራቸው ለነጭ ቀለም ከፍተኛ ትኩረትና ምርጫ ሰጥተዋል።

ኡስታዝ ፉአድ አብዱ  የእስልምና ኃይማኖት መምህር ናቸው፡፡ በእስላማዊ ትምህርት ጥናት በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትምህርታቸውን እየተማሩና  ሌሎችንም እያስተማሩ ነው፡፡ “ነብዩ መሐመድ ቀለምን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጧቸው ነገሮች አሉ” ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ “ከልብሶቻችሁ ነጭ ልብሶችን አብዝታችሁ ልበሱ፤ እሱ ከልብሶቻችሁ ሁሉ በላጭ (ጥሩ) ነውና” የሚለው ዋነኛው ነው የሚለውን ይጠቅሳሉ፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ነጭ ልብስን የመረጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ “እሱ ይበልጥ ንጹህና ያማረ ነው” ብለዋል። ነጭ ልብስ ላይ ጥቃቅን ቆሻሻዎች እንኳን ወዲያው ስለሚታዩ፣ ሰውየው ልብሱን ቶሎ እንዲያጥብና ሁልጊዜም ንጹህ ሆኖ እንዲቆይ ያደርገዋል። ይህ ውጫዊ ንጽህና ደግሞ የውስጥ (የልብ) ንጽህና ማሳያና መዳረሻ ተደርጎ ስለሚሰወሰድ ነው ይላሉ፡፡

ነጭ ቀለም ያለው ልብስ ዋነኛ ትኩረቱ ንጽህና ነው፡፡ የአካል ንጽህና ነጸብራቁ የልብ ንጽህና መገለጫ ሆኖ ይታያል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ልብሳቸው ነጽቶ ውስጣቸው ሊቆሽሽ ይችላል። ነገር ግን ሰው ላዩን ንጹህ ባደረገ ልክ ደግሞ ልቡን ንጹህ የማድረግ ሁኔታው ይጨምራል፡፡ እና በዋናነት የሚፈለገው እና ዓላማው ውስጥን እንደ ነጭ ቀለም ንጹህ ማድረግ ነው በማለት ኡስታዝ ፉአድ ያብራራሉ፡፡

በእስልምና ትልቁ የአምልኮ ሥነ-ስርዓት በሆነው በሐጅ (የመንፈሳዊ ጉዞ) ወቅት፣ ከዓለም ዙሪያ የሚሰበሰቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ያሉበትን የሀብት፣ የስልጣን፣ የዘር እና የባህል ልዩነት በሙሉ ትተው ተመሳሳይ ነጭ ልብስ ይለብሳሉ። ይህም በፈጣሪ ፊት ሁሉም ሰው እኩል መሆኑን፣ ንጉስም ሆነ ምስኪን፣ ነጭም ሆነ ጥቁር ልዩነት የሌላቸው አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ታላቅ የተምሳሌት ቀለም ነው።

እንዲሁም የአርብ ቀን (ጁሙዓ) ለሙስሊሞች የሳምንቱ ታላቅ የጋራ የአምልኮ ቀን ነው። በዚህ ቀን ወደ መስጂድ ከመሄድ በፊት ገላን መታጠብ፣ ሽቶ መቀባት እና ንጹህ ነጭ ልብስ መልበስ እጅግ የተወደደ ነው። ይህም ለዕለቱ የሚሰጠውን ክብርና መንፈሳዊ ዝግጅት ያሳያል።

የአል ኢምራን ቁራን አካዳሚ መስራች ወጣት ኑራዲስ ሰኢድ በበኩሉ፤ ነጭ ቀለምና ልብስ በእስልምና አስተምህሮ በህይወት ብቻም ሳይሆን እስከ ሞት ድረስ የተመረጠ ቀለም ነው በማለት ያስረዳል፡፡ ወጣቱ “ሙታኖቻችሁንም በነጭ ልብስ ከፍኑ”  የሚለውን የነብዩ መሐመድ ቃል  ነጭ ቀለም በእስልምና ኃይማኖት ውስጥ ያለውን ትልቅ ስፍራ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሷል።

በእርግጥም የነጭ ቀለም ክብርና አገልግሎት በሰው ልጅ ህይወት ብቻ የሚያበቃ አይደለም። አንድ ሙስሊም ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ፣ አስከሬኑ (ጀናዛው) ታጥቦ ወደ ቀብር ከመወሰዱ በፊት የሚከፈነው በነጭ ጨርቅ ነው። ይህም ሰውየው ወደ አኺራ (ወደሚቀጥለው ዓለም) ሲሄድ ንጹህ ሆኖ እንዲሄድ ካለው ምኞትና አስተምህሮ ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ ነጭ ቀለም በእስልምና ኃይማኖት ውስጥ የንጽህና፣ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የእኩልነት እና የመንፈሳዊ ከፍታ ትልቅ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

አረንጓዴ

በእስልምና አስተምህሮ እና ባህል ውስጥ አረንጓዴ ቀለም እጅግ የላቀ፣ የተከበረና ልዩ ቦታ ያለው ሌላኛው ቀለም ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በቀጥታ ከቅዱስ ቁርዓን አንቀጾች፣ ከነብዩ  አስተምህሮና ተግባር እንዲሁም ከጀነት (ገነት) መገለጫዎች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው።  ከዚህ በተጨማሪ ነብዩ መሐመድም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ አረንጓዴ  ልብስ ለብሰው ታይተዋል ይላሉ ኡስታዝ ፉአድ።

ከነብዩ መሐመድ  ልብሶች መካከል አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ልብሶች  ነበሩ፡፡  እነዚህን ልብሶች ይወዱና ይለብሱ እንደነበር በሀዲሶች ተዘግቧል። ሰሃባዎችም  ውብ አረንጓዴ ልብስ ለብሰው እንዳዩአቸው መስክረዋል። ስለዚህ ሙስሊሞች ይህንን ቀለም መልበስ የነብዩን ሱና እንደመከተል አድርገው ይቆጥሩታል።

ኡስታዝ ፉአድ እና ወጣት ኑራዲስ ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት የጀነት ሰዎች ከሐር የተሰሩ አረንጓዴ ልብሶችን እንደሚለብሱ እና አረንጓዴ መደገፊያዎችን እንደሚደገፉ እንዲሁም ውብ በሆኑ ምንጣፎች ላይ እንደሚቀመጡ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በተፈጥሮም አረንጓዴ ቀለም ተፈጥሮን፣ ልምላሜን፣ ህይወትን፣ እድገትን እና የተፈጥሮን ውበት (ለምሳሌ ዝናብ ሲዘንብ መሬት በአረንጓዴ ዕፅዋት መሸፈኗን) ያሳያል። እስልምና ደግሞ የህይወትና የሰላም ኃይማኖት በመሆኑ፣ ቀለሙ ከእምነቱ መንፈሳዊ እሴቶች ጋር  ይጣጣማል።

እንዲሁም በታሪክም ሆነ በአሁኑ ዘመን በርካታ የሙስሊም አገሮችና ተቋማት በሰንደቅ ዓላማዎቻቸው፣ በባህላዊ አልባሳቶቻቸው፣ በመንፈሳዊ ሥነ ስርዓቶች እና  በመንዙማና ነሺዳ ሥነ ሥርዓቶች ላይ አረንጓዴ ቀለምን በስፋት ይጠቀማሉ።

በአጠቃላይ፣ አረንጓዴ ቀለም በእስልምና ውስጥ የንጽህና፣ የሰላም፣ የህይወት እና የጀነት ተስፋ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ልዩ ውበትና ክብር አለው፡፡

ጥቁር ቀለም

በእስልምና ኃይማኖት ውስጥ ቀለማት የላቀ ቦታና የየራሳቸው የሆነ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ትርጉም አላቸው። ከእነዚህ ቀለማት መካከል ጥቁር ቀለም አንዱ ሲሆን፣ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ሰፊ ስፍራና የተለየ ትርጓሜ የሚሰጠው ቀለም ነው። በአንዳንድ ባህሎች ውስጥ ጥቁር ቀለም ከሀዘን ወይም ከክፉ ነገር ጋር ብቻ ተያይዞ ቢታይም፣ በእስልምና አስተምህሮ ግን ከፍ ያለ ክብርና ውበትን የሚወክልበት በርካታ አውዶች አሉ።

ነብዩ መሐመድ በተለያዩ ሁኔታዎች ጥቁር ቀለማት ያላቸውን አልባሳት ለብሰዋል፡፡ ለአብነትም ጥቁር ጥምጣም ይለብሱ እንደነበር በሐዲስ ተዘግቧል። ጥቁር ሰንደቅ ዓላማ (መለያ ምልክትም) ተጠቅመዋል፡፡ ምክንያቱም ጥቁር የክብር፣ የቁም ነገርና የልግስና ምልክት ነው ይላሉ ኡስታዝ ፉአድ።

በአጠቃላይ በእስልምና ከፍ ያለ ቦታ የተሰጣቸው ቀለማት ከላይ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ በእስልምና ኃይማኖት ውስጥ በተለየ ሁኔታ የሚወደዱ ቀለማት ቢኖሩም “የማይፈቀድ” ተብሎ የተበየነ  ወይም የተፈረጀ ቀለም የለም፡፡ ምክንያቱም ቀለማት በሙሉ የአላህ (ፈጣሪ) የፍጥረት ውበት መገለጫዎች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው።

ጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review