ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰድነው የምርጫ ካርድ ድምፅ ለመስጠት ተዘጋጅተናል – የመዲናዋ ነዋሪዎች

AMN ግንቦት 19/2018

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት የምርጫ ካርድ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ድምፅ መስጫ ቀን ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በተለያዩ ምዕራፎች በማካሄድና በማራዘም ከየካቲት 28 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

በዲጂታል “ምርጫዬ” መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎቹ በአካል በመገኘት የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ከ50 ሚሊየን 514 ሺህ በላይ ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ በዜጎች የነቃ ተሳትፎ የሚካሄድ ሀገራዊ ምርጫ በዴሞክራሲ ሥርዓት የፀና ሀገረ መንግስት ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የመዲናዋ ነዋሪና በአዲስ አባባ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ብጽዕት ንጉሴ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላትን ካርድ በመውሰድ ዕለቱን እየተጠባበቀች መሆኗን ገልጻለች።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሳምሶን ፍስሃ እንደሚሉት፤ ምርጫ የጠንካራ ሀገረ መንግስትና የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንቢያ መሳሪያ ነው።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም የምርጫ ካርድ በመውሰድ ድምፅ በሚሰጥበት ዕለት ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራል ብለው ለሚያምኑት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት የመራጭነት ካርድ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ ሶፍያ ከድር ናቸው።

ሀገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጠናከርበትና የዜጎች የመምረጥ መመረጥ መብት በተግባር የሚታይበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ስሜ በቀለ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊና የተሻለ የዴሞክራሲ ልምምድ እየታየበት የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ማስረሻ ንጉሴ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ የዴሞክራሲ ምኅዳር መሠረት የሚጣልበት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የሀገርን ዕድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲ አማራጭ ላለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ያሬድ ታደሰ በበኩሉ፤ ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በወቅቱ በመውሰድ ድምፅ መስጫዋን ዕለት እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ማስታወቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review