ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ግንባታ ትልቅ ተስፋና መነቃቃትን ፈጥሯል

You are currently viewing ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ግንባታ ትልቅ ተስፋና መነቃቃትን ፈጥሯል

AMN – ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር በዜጎች መካከል ታላቅ ተስፋን መፍጠሩንና ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ።

መመካከርና መደማመጥ ስር የሰደዱና ዘመናዊ ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው መንገድ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎች፣ በምክክር ሂደቱ የሚገኙ የጋራ መፍትሄዎችንና ሀገራዊ ፋይዳዎችን በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በተለይም በጦርነት ውስጥ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንደማይኖር በመጠቆም፣ ሀገርን ማሻገር የሚቻለው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ የሃሳብ የበላይነት ውይይት ብቻ መሆኑንና አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ዝግጅት የተባበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደቱ ላይ አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን የሰጡ ዜጎች እንደገለጹት፤ ምክክሩ የጋራ እሴቶችን ይበልጥ ለማዳበርና እርስ በርስ ለመደማመጥ ታላቅ ዕድል የፈጠረ ነዉ።

ይህም የአንዱን ድምፅ አጥፍቶ የሌላውን ብቻ ይዞ መውጫ ሳይሆን እርስ በርስ የተናበበ ቋንቋና ባህላዊ ትውፊቶችን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

በመነጋገር የተስማሙባቸውን ነጥቦች ማጽናትና ልዩነቶች ሲኖሩም በመከባበርና የሌላውን ሃሳብ በመቀበል መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሀገራችንን ችግሮች በመወያየትና መፍትሄ በመስጠት፣ ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊት ሀገር ለማውረስ ዛሬ የሚጣለው ታሪካዊ አሻራ እጅግ የጎላ መሆኑም ተመላክቷል።

ምክክሩ በታሪክ ላይ ካለው ከፍተኛ ፋይዳ አንጻር ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጊዜ ባይፈታ እንኳ፣ ጠንካራ ህብረ-ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለመተሳሰር ትልቅ በር እንደሚከፍት ተሳታፊዎቹ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

ቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊት ሀገርን እንዲረከብ ቁርሾዎችን በመተው የተሻለች ሀገር መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ በነጻነት ተገናኝቶ የመወያየት ልምድ እንዳልነበረ ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁን ግን ይህንን ዕድል ለመጀመሪያ ጊዜ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review