ትውልዱ የአድዋ ድልን አረንጓዴ አሻራውን በማኖር ሊደግመው ይገባል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን በአድዋ ድል ያስመዘገቡትን ድል የአሁኑም ትውልድ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተባብሮ ችግኝ በመትከል የራሱን የጀግንነት አሻራ ሊያኖር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህንን ያሉት የዘንድሮውን ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መርኃ ግብሩ በቢሾፍቱ እንዲጀመር የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ከተማዋ በኮሪደር ልማት ሥራ ብቻ ሳይሆን ዛፍና አበባ በመትከል እንዲሁም ችግኝ በማፍላት ለራሷም ሆነ ለአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ የግብዓት ምንጭ በመሆኗ እንደሆነ አመላክተዋል።

በተጨማሪም ለዚህ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ለማቅረብ ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የአረንጓዴ አሻራ ልማት በቀጥታ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብልጽግና ከማረጋገጥ ብሔራዊ ህልም ጋር የሚተሳሰር አንኳር ጉዳይ መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል።

በመሆኑም ትውልዱ ጀግኖች አባቶች ያወረሱትን ነጻ ሀገር አረንጓዴ በማልበስ ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ሳታውቀው ያጣችው የአፈር መጠን በገንዘብ ሊተመን የማይችል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ጠቃሚ አፈር ከመሸርሸርና የሌሎች ሲሳይ ከመሆን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ይህንን ተረድቶ ችግኝን ሊተክል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review