AMN – ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና አሰራርን ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር ለማላቀቅ በርካታ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ ዲጂታል ማዕከል የማስገባት ዝግጅት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በተለይም ከገቢ ጋር የተያያዙ በርካታ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ ዲጂታል ማዕከል ለማስገባት መታቀዱን የገለጹት ከንቲባዋ፣ አመራሩም በ90 ቀን እቅዱ ውስጥ ለዚህ ዝግጅት ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ በመድረኩ ለተገኙ አመራሮች አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ከንቲባ አዳነች አክለውም ከዚህም በተጨማሪ ከግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ስራ ጋር ተያይዞ ህዝቡን የሚያማርሩ፣ ግለሰቦች ሲፈልጉ የሚከፍቱትንና ሲፈልጉ የሚዘጉትን የኦንላይን አሰራሮች በማስቀረት ረገድ ማዕከሉ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል።
አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የንግድ አገልግሎቶችንም ወደ ዲጂታል ማዕከሉ የመጨመር ፍላጎት እንዳለ ከንቲባ አዳነች አመላክተዋል፡፡

ይህንን አሰራር በማጠናከር አብዛኛውን አገልግሎት ወደ አንድ ዲጂታል ማዕከል እያስገቡ መሄድ፣ ሰውን ማሰልጠንና ማብቃት አገልግሎቱን ከብዙ ውጣ ውረድና ከሌብነት ብሎም ከብልሹ አሰራር ለማላቀቅ ዋነኛው መንገድ እንደሆነ ከንቲባዋ አብራርተዋል።
ከንቲባ አዳነች በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ላለው ለውጥና ከተማዋን መልሶ ለማልማት ለተገኘው ሀብት መሶብ ዲጂታል ማዕከል አንዱ ትልቁና ዋነኛው ማሳያ መሆኑም በመድረኩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ በትክክል የተሰሩ ስራዎችንና የመጡ ለውጦችን በሚገባ ለህዝብ ማሳወቅ እንደሚገባ የገለጹት ከንቲባዋ፣ አመራሩም በዋናነት የተደራጀ መንገድ በመከተል የስራ ውጤታማነትንና ቀጣይነትን ይበልጥ ማረጋገጥ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በወርቅነህ አቢዮ