AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሰላም ሰራዊት አባላትና ማህበረሰቡ ያደረገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሰላም ሰራዊት፣ ከፓሊስና ደንብ ማስከበር ጋር በመተባበር ለአካባቢው ሰላም ብሎም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረጉትን ተሞክሮ ተመልክቷል፡፡
የሰላም ሰራዊቱ ከአጎራባች ሸገር ከተማ ቀበሌዎች ጋር በመሆን ለአካባቢው ሰላም ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚደነቅና ምስጋና የሚቸረው ስለመሆኑ የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በላይ ደጀን ናቸው፡፡

አቶ በላይ ደጀን፤ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደነበረ አውስተው አሁንም ማህበረሰቡ ሰላምን ለማደፍረስ ከሚጥሩ አካላት አካባቢውን መጠበቅ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በበኩላቸው፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ዘርፍ አካላትና የጥምር ኃይል ፖሊስ አባላት፣ ደንብ ማስከበር ኦፊሰሮችንና የሰላም ሰራዊቱ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
በመርኃ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህዝብ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ጥበቡ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በየሺዋስ ዋለ