በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ልዩነቶችን በውይይትና ምክክር መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ልዩነቶችን በውይይትና ምክክር መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ

AMN – ሰኔ 21/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶችና ምክክሮች መፍታት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፤ በኢትዮጵያ ግጭቶችንና ልዩነቶችን በሰላማዊ የውይይትና ምክክር መድረክ የመፍታት ልማድ ሊጎለብት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ያለ ምክክርና ውይይት የምትጓዝ ሀገር መጨረሻዋ ግጭትና ከፍተኛ ሀገራዊ ኪሳራ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ መላው ህዝብ ከግጭት ይልቅ ለምክክርና ውይይት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግሮችን በየደረጃው በሚደረጉ ምክክሮች መፍታት የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ዋነኛውና ቁልፍ መሣሪያ በመሆኑ ይህ በጎ ባህል ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላምን እና ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘረኛና ጽንፈኛ እሳቤዎችን በጋራ ሊታገል እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ዘረኛና ጽንፈኛ እሳቤዎች ሰላምን በማደፍረስና ግጭትን በማባባስ ረገድ ያላቸው ድርሻ የላቀ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር እነዚህን ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መግራት ይጠበቃል፡፡

ዘረኛና ጽንፈኛ እሳቤ ለአንድ አካል ወይም ወገን ብቻ የሚተው፣ ወይም ራስን ነጻ አድርጎ ሌላውን ለመውቀስ የሚደረግ ጉዳይ ሳይሆን በተለያዩ ግለሰቦች ሊንጸባረቅ የሚችል የአስተሳሰብ ችግር በመሆኑ፣ መላው ህብረተሰብ እነዚህን ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች በጋራ ሊታገል ይገባልም ብለዋል፡፡

በቅድሚያ ራስን ከጽንፈኛና ዘረኛ እሳቤዎች ማላቀቅና ሌላውም ከዚህ እሳቤ ነጻ እንዲሆን መምከር ተገቢ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ራስን ከዚህ እሳቤ ነጻ ሳያወጡ ሌላኛውን ብቻ ለመውቀስ መሞከር ተገቢ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጽንፈኛና ዘረኛ እሳቤዎች በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ፣ በማህበራዊ ኑሮና በተቋም ደረጃ የሚያስከትሉት አደጋ የከፋ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ ዜጋ እነዚህን እሳቤዎች በመታገል የወንድማማችነትንና የአብሮነት መንፈስን ሊገነባ ይገባል ሲሉ ነዋሪዎቹ አስገንዝበዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review