AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ከጥላቻ እሳቤ ነጻ በመሆን በሃገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን አንድነት፣ እድገትና ሰላም መገንባት ይኖርብናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነት እና እድገት እንዲሁም ሰላምን ለመገንባት ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጋ ያሳተፈና ያቀፈ ሃገራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ያነጋገራቸው አቶ ሙራድ ሸሪፍ፤ ኢትዮጵያውያን የቆዩ ችግሮቻችንን ተነጋግረን በመፍታት በጋራ መኖር አለብን ብለዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሃገራዊ ምክክር ጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ በማንሳት በቀጣይም ያሉ ችግሮች ላይ በመምከር ኢትዮጵያን ማሳደግ ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

አቶ አምሃ እጓለ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለውን ስራ በዚህ ከቀጠለ እና እንደ ሃገር ያሉ ችግሮችን ለይቶ ሰላምን ለመገንባት ሁኔታዎችን ካመቻቸ ፍሬያማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በዚህም እንደ ሃገር በሁሉም አካባቢ ዘላቂ ሰላም ሲኖር አዲስ አበባ ላይ የሚታዩ የልማት ሥራዎችን በሌሎች አካባቢዎችም በሰፊው ማከናወን እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አምሃ፤ በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባቶችን፣ ልዩነቶችን ማስወገድ የሚቻለው በሃይል ሳይሆን በውይይት እንደሆነ ጠቅሰው በምክክር የኢትዮጵያን አንድነት፣ እድገትና ሰላም መገንባት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሃገር የለንም፣ ኢትዮጵያ ሰላም ሆና እንድትቀጥል፣ ለልጆቻችን የተከበረች ሃገር ለማስረከብ፤ የሃሳብ ልዩነቶች ላይ መነጋገር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ ኤልያስ ባልቻ ናቸው፡፡
በብሄር፣ በሐይማኖት መጋጨት ለማንም አይጠቅምም፣ አንዱ ለአንዱ ውበትና ጌጥ በመሆኑ ከጥላቻ እሳቤ ነጻ መሆን አለብንም ብለዋል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ይህ የምክክር ሂደት፣ ልዩነቶችን በምክክር ፈትቶ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ዕድል እንደሆነ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ሕዝብ የምክክር ጉባኤ” ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ እንደሚጀመር መገለጹ ይታወሳል።
የሻምበል ምህረት