AMN – ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
የሃይማኖት ተቋማት የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ሂደት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማጽናት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተፈራርመውታል።
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
ፖሊስና የሃይማኖት ተቋማትም ኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር በቅርበትና በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ስምምነቱም የሀገርን ዘላቂ ሰላም የበለጠ በማጠናከር ውጤታማ ሥራ ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በተለይም ሊከሰቱ የሚችሉ የሰላምና ደህንነት ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
የሀገር ሰላም ተከብሮ፣ ልማቷ አድጎና ሕዝቧ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆን ዋናው መሠረት ሰላም መሆኑን አንስተው፤ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ አጋዥና ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የተደረገው ስምምነት ሁለቱ ተቋማት ይበልጥ ተቀራርበው ሰላምን ለማጽናት እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል የሀገርን ሰላምና ደህንነት እያስከበሩ ነው ብለዋል።
ሰላም የጋራ ዕሴት ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ከፖሊስ ጋር በመተባበር ለሀገር ሰላም ግንባታ የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ስምምነቱም ትብብርና ቅንጅትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በዚሁ ጊዜ የሀገርን ሰላም ለማስከበር ፖሊስ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝና የጋራ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ፤ ፖሊስ ለሀገር ሰላም ሲል ቀንና ሌሊት የሚሠራውን ሥራ በማድነቅ፣ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለፖሊስ የሚያደርጉትን እገዛና ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ነብርእድ ኤሊያስ አብርሃ፤ የሃይማኖት ተቋማት እስካሁን በሰላም ጉዳይ ላይ በትኩረት ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው፣ የዛሬው ስምምነት ሥራውን ይበልጥ ጠንካራ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጄ ጀንበሩ፤ ስምምነቱን ከመተግበር አንጻር በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለሰላም ምሳሌ መሆን እንደሚገባም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡