AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤምባሲዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ለዘላቂ ልማት ትልቅ ድርሻ እንዳበረከተ ገልጸዋል።
ይህ ጥረት የካርቦን ልቀትን በመቀነስ የውሃ ተፋሰሶችን በመጠበቅ እና የዱር እንስሳት መኖሪያዎችን በመታደግ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ የሚሰጥ ብሔራዊ ቁርጠኝነት መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በፓሪስ ስምምነት መሰረት ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት እና ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ጽኑ አቋም በተግባር እያሳየች ነውም ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሀደራ አበራ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ ለ2027 ዓ.ም የሚዘጋጀውን COP32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤን ስትጠባበቅ የዛሬው የጋራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እንቅስቃሴ ትልቅ እመርታ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮች እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እያደረገች ያለችው ጥረት አርዓያነት ያለው ነው።
ሌሎች የዓለም ሃገራት ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ በተጨባጭ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው በመግለጽ ይህም ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

የዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዓላማ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ትስስርን ማጠናከር እና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገርን የማስረከብ የጋራ ራዕይን የሚያንፀባርቅ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስቀመጡትን 8 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ብሔራዊ ግብ ለማሳካት የዛሬው የዲፕሎማቶች ተሳትፎ የጋራ የአካባቢ ኃላፊነትን በተግባር ያሳየ ሆኗል።
ተሳታፊዎቹም በመርሐ ግብሩ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በሄቨን እያዩ