የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዓለም ቁንጮ ተጓዦች ከተመረጡ 5 ምርጥ የዩኔስኮ ቅርሶች መካከል ተካተተ

You are currently viewing የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዓለም ቁንጮ ተጓዦች ከተመረጡ 5 ምርጥ የዩኔስኮ ቅርሶች መካከል ተካተተ

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

በዓለም ላይ ያሉትን ሀገራት በሙሉ በመጎብኘት “UN Grandmaster” የተባለውን ታዋቂ የክብር ማዕረግ ያገኙ የዓለማችን ቁንጮ ተጓዦች፣ የሚመክሯቸውን ምርጥ የጉዞ መዳረሻዎች ይፋ አድርገዋል።

በታዋቂው የዜና አውታር ‘ዩሮኒውስ’ (Euronews) በተደረገ ጥናት፣ እነዚህ ሁሉንም የዓለም ክፍሎች ያዩ አንጋፋ ተጓዦች ካስቀመጧቸው ተወዳጅ የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በግንባር ቀደምትነት ከምርጥ 5 ውስጥ መካተት ችሏል።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠ ምስክርነት፣ ኢትዮጵያ አስደናቂ ታሪክና አስገራሚ ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆኗን በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።

ተጓዦቹ እንደ አንኮር ዋት እና ታላቁ የቻይና ግንብ ካሉ ታዋቂ ቅርሶች ጎን ለጎን የላሊበላን ድንቅ የጥበብ ጥልቅነት እና መንፈሳዊ ግርማ ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ሊታይ የሚገባው ቀዳሚ የጉዞ ዕንቁ መሆኑን ያሳያል።

መንግሥት ይህንን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ይበልጥ ለማጎልበት የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከማንኛውም ዓይነት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እንዲሁም ከዘላቂ የቅርስ ልማትና ጥበቃ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የቅርስ ጥበቃ ሥራዎችን ከዘመናዊ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በማቀናጀት፣ አካባቢው ለጎብኚዎች ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማሳደግ መንግሥት በትጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review