AMN- ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ በካይ ጋዝ የምትለቅ፣ ነገር ግን ሰፊ የደን ሃብትና ታዳሽ ኃይል ያላት ሀገር በመሆኗ በዓለም አቀፉ የካርቦን ገበያ ላይ ተመራጭ የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ መሆኑ ይገለፃል።
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በተለያዩ በሰርቶ ማሣያ ፕሮጀክቶች አማካኝነት በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ማግኘት መጀመሯን ይፋዊ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የዓለም ባንክ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ሀገሪቱ የካርበን ንግድን በይፋ ለመምራት የሚያስችል ብሔራዊ የህግ ማዕቀፍ እና መመሪያዎችን ያዘጋጀች ሲሆን፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበርም አስተማማኝ የካርበን ክሬዲት ምዘገባና ቁጥጥር ሥርዓት ዘርግታለች።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉበት ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እና ሀገሪቱ የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል 100 በመቶ በሚባል ደረጃ ከታዳሽ ኃይል ማለትም ከውሃ፣ ከንፋስ እና ከእንፋሎት (ጂኦተርማል) መሆኑ ለወደፊቱ የካርቦን ንግድ እጅግ ግዙፍና ተፈላጊ የአቅርቦት አቅምን እየፈጠረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ገና በጅምር ላይ ብትሆንም፣ በተለያዩ የሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ አጋርነት ፕሮጀክቶች አማካኝነት በተግባር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በኢትዮጵያ ትልቁና ስኬታማው የባሌ ተራሮች የደን ጥበቃ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የባሌን ብሔራዊ ፓርክና አካባቢውን ደን በመጠበቅ የተገኘውን የካርበን ክሬዲት ለዓለም አቀፍ ገዢዎች በመሸጥ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ገቢ ማስገኘት ችሏል።

በተመሳሳይ በወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ የተተገበረውና ከዓለም ባንክ ጋር የተሰራው ፕሮጀክት፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የመጀመሪያው በተባበሩት መንግስታት እውቅና አግኝቶ የካርበን የካርቦን ልቀት ማካካሻ (ሽያጭ) የተከናወነበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ሆኖ ተመዝግቧል።
ፕሮጀክቱ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬትን በማገገም፣ በአየር ንብረት ፋይናንስ የአካባቢውን ህብረተሰብ ህይወት መቀየር እንደሚቻል በአርአያነት የሚጠቀስ ሥራ አሳይቷል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር አሁንም ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጓት ሳይንሳዊና መዋቅራዊ ፈተናዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሀገሪቱ ክሬዲቶቿን የምትሸጠው በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተው ገበያ በመሆኑ የምታገኘው ዋጋ በአንድ ቶን ከ5 እስከ 10 ዶላር ብቻ መሆኑ አንዱና ዋናው ፈተና ነው።

በተጨማሪም በአንድ ደን ውስጥ ምን ያህል ካርበን እንደተመጠጠ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማለትም በሳተላይትና በሪሞት ሴንሲንግ ለክቶ ለዓለም አቀፍ ገበያ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ማቅረብ ከፍተኛ እውቀትና ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚሳተፉ የሀገር ውስጥ ድርጅቶችና የአርሶ አደር ማህበራት ዘንድ ስለ ካርቦን ንግድ ዘመናዊ አሰራር ያለው ግንዛቤ አሁንም ውስን መሆን በዋናነት ተጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በካርበን ንግድ ረገድ በአሁኑ ወቅት በትክክለኛ መስመር ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በባሌ እና በሁምቦ የተገኙት ተሞክሮዎች በተግባር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ማረጋገጫዎች ናቸው።
ወደፊትም አዳዲስ የካርበን ገበያ አዋጆች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡና የዓለም አቀፉ የካርበን ዋጋ በድርድር ሲሻሻል ሀገሪቱ የምታገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
በአስማረ መኮንን