AMN- ሰኔ 25/2018ዓ.ም

ቱሪዝም ከነዳጅና ከኬሚካሎች በመቀጠል፤ እንዲሁም ከምግብና ከአውቶሞቲቭ ምርቶች በመቅደም በዓለም ሶስተኛው ትልቁ የውጭ ንግድ ኢንዱስትሪ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያም በመደመር እሳቤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማት ጀምሮ ያሏትን የቱሪዝም መስህቦችን በማስተዋወቅ የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

ህብረተሰቡ ሀገሩንና አካባቢውን እንዲያውቅ እና እንዲጎበኝ በማደረግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማበረታታት እየተሰራ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ዜጎች ለሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወርና በመጎብኘት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕድ የሚገባትን ድርሻ እንድትቋደስ እየተደረገ ባለው ብርቱ ጥረት አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና ሁነቶችን ጨምሮ ፈቃደኛ ሆነው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኚዎች ምርጥና የማይረሱ ጊዜአትን እንዲያሳልፉ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህም በርካታ የአፍሪካና የዓለም መሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ ስፓርተኞች እና ሌሎች የውጭ ሀገራት ዜጎች አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎችንና ከተሞችን መጎብኘት ችለዋል፡፡
የአፍሪካ መዲናና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በተለይ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የተገነቡ መሰረተ ልማቶች እና የቅርስ ልማትና ጥበቃ ሥራዎች የመዲናዋን አጠቃላይ ገጽታ ከመቀየራቸው በተጨማሪ በርካታ ቱሪስቶች ውሎና አዳራቸውን በአዲስ አበባ እንዲያደርጉ አስገድደዋቸዋል፡፡

የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በመዲናዋ የተገነቡ አማራጭ የቱሪዝም መስህቦች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ፓርኮች፣ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች እንዲሁም የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነትና የመዲናይቱ አስተማማኝ ሰላም ቱሪስቶች አዲስ አበባን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው እንዲመለከቱ አስችሏቸዋል፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው የሀገራት መሪዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች የውጭ ሀገራት ዜጎችም የኢትዮጵያ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆን በቀጥታ ስርጭት እና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ስለ ሀገሪቱ ድንቅ የቱሪዝም መስህቦች፣ እንግዳ ተቀባይነትና ሰላማዊነት በደስታ መስክረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ቱሪዝም – አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል ባደረጉት ቃለመጠይቅ፣ የጎብኚዎችን ቁጥር እና ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉ በርካታ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ከ1.4 ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን እና ይህ ቁጥር ከካች አምናው አንጻር የ300 ሺህ እንዲሁም ካለፈው ዓመት አንጻር የ100 ሺህ ቱሪስቶች ቁጥር ጭማሪ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ዘንድሮ ከ 5.4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ
See less