AMN ሰኔ 26/2018
የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝምን የኢኮኖሚ መሰሶ በማድረግ የሚያከናውነው አስደናቂ ኢንቨስትመንት ዕድገትን የሚያፋጥን መሆኑን በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዩኔስኮ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት (ዶ/ር) ገለጹ።
ታሪካዊው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዓለም አምስት ምርጥ ዩኔስኮ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ መመረጡንም አስታውቀዋል።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማክ ልዑካን ቡድን አባላትም የዓለም ቅርስ የሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዩኔስኮ ተወካይ ሪታ ቢሶናውት (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የላሊበላ ጥንታዊ ስልጣኔ የዓለምን ቀልብ የሚስብ ድንቅ ሥራ ነው።
ዩኔስኮም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ውበትና የስልጣኔ መገለጫ ቅርሶች እንዲገነዘብ ለማስቻል በተለያዩ ጊዜያት የጉብኝት መርሃ ግብር እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡም ወደ 100 የሚጠጉ የውጭ ሀገር እንግዶችን ወደ ኢትዮጵያ በመጋበዝ የጉብኝት መርሃ ግብር መካሄዱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመተባበር በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚያከናውነው የታሪካዊ ቦታዎች ዕድሳትና ጥገና ሂደት አስደናቂ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝምን የኢኮኖሚ መሰሶ በማድረግ የሚያከናውነው አስደናቂ ኢንቨስትመንት ዕድገትን የሚያፋጥን አቅም መፍጠሩንም ተናግረዋል።
ለዚህም እንደወንጪና ጨበራ ጩርጩራ ያሉ አስደናቂ አዳዲስ የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎች መገንባታቸው የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያን የቱሪዝም የገቢ አቅም በማሳደግና የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስፋት አቅም እየፈጠረ መሆኑን ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።