በዘንድሮዉ ጠቅላላ ምርጫ ጽንፈኝነትን ፤ ባንዳነትን እና ዘረኝነትን አንፈልግም፤ ምኞታችን ተባብረን የጋራ ሃገር ማጽናት ነዉ የሚሉ ድምጾች በአንድነት ተስተጋብተዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing በዘንድሮዉ ጠቅላላ ምርጫ ጽንፈኝነትን ፤ ባንዳነትን እና ዘረኝነትን አንፈልግም፤ ምኞታችን ተባብረን የጋራ ሃገር ማጽናት ነዉ የሚሉ ድምጾች በአንድነት ተስተጋብተዋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ ከመራጮች እና ከምርጫ ሂደት ጋር በተያያዘ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ የዘንድሮው ምርጫ በተለየ ሁኔታ ሕዝቡ ከፍተኛ ማስፈራሪያዎች ቢደርሱበትም፣ እነርሱን በመቋቋም ከ50 ሺህ በላይ በሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች በነቂስ በመውጣት ታይቶ የማይታወቅ ተሳትፎ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የዘንድሮ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተለየ፣ ምርጫውን ራሱን እንደ ኢላማ በመውሰድ ሊያስተጓጉሉት የሞከሩ ኃይሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ አካላት ሃሳብ እና ውይይትን ከመምረጥ ይልቅ የጉልበት አቅምን ለመጠቀም መሞከራቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ግን በምርጫው ወቅት “ጽንፈኝነትን፣ ባንዳንነትን እና ዘረኝነትን አንፈልግም” በሚል በአንድ ድምፅ አቋማቸውን ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

በመላው የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የሚስተዋለው ይህ የአንድነት ድምፅ፣ አረጋውያን፣ እናቶች እና በየደረጃው ያሉ ዜጎች ለወደፊቱ ትውልድ ሲባል በከፍተኛ ተነሳሽነት መሳተፋቸው የሕዝቡን አደራ የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህ ታላቅ የሕዝብ ተሳትፎ ለመንግሥት ትልቅ አደራ እና ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሕዝቡ ለመንግሥት የሰጠው ድጋፍ ለዕቅዶች ስኬት እና ለሥርዓታዊ ሌብነት መጥፋት ያለውን ተስፋ እንደሚያመለክት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ብልፅግና ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ቀናነት በማሰብ፣ ከምርጫው በፊት በነበረው ውይይት ከ85 በመቶ በላይ በሆኑ ወንበሮች ላለመወዳደር መወሰኑን አስታውሰዋል።

ገዢው ፓርቲ 15 በመቶውን ድርሻ ለሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በመተው፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰደው ይህ እርምጃ፣ በአፍሪካ ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየውን ተሳትፎ እና የሰጠውን አደራ መንግሥት በታላቅ ኃላፊነት እንደሚቀበለው ገልጸው፣ የፀናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሥራት የሁለቱም ወገኖች ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review