AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ የትርክት ስብራቶችንና ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመፍታትና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እየተጫወተ ያለውን ሚና በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግሥት ለብሔራዊ ምክክሩ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት በርካታ የሕዝብ ውይይት መድረኮች በየደረጃው እንዲካሄዱ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የውይይትና የምክክር መድረኮች በሀገሪቱ ስር ሰደው የነበሩ ግጭቶችን በማስቆም ረገድ የሰላም መንገዶች እንዲታዩ ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ የጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን መደራደሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያሳተፈ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው ብለዋል፡፡
መድረኩ ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ ያሉ ዜጎች ስለ ሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያለምንም ስጋት በነጻነት የሚወያዩበትና የራሳቸውን አጀንዳ የሚሰጡበት ታሪካዊ ምህዳር መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ብዙዎች ለረጅም ጊዜ የጠየቁትና ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉበት መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያውያን ይህን ታላቅ ሀገራዊ ሂደት ማሳነስ እንደማይገባቸው በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

የምክክሩ ሂደት በፍጥነትና በችኮላ የሚከናወን ሳይሆን፣ በጥናትና በትዕግሥት እንዲመራ አስፈላጊው ጊዜ እየተራዘመለት በጥንቃቄ እየተከናወነ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አስረድተዋል፡፡
በአስማረ መኮንን