AMN- ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደራቸውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት አብዮት መካሄዱንና በ24/7 አዲስ የሥራ ባህል ጀምሮ የመጨረስና ጨርሶ የመጀመር ልህቀት የተመዘገበበት ታሪካዊ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የቻሉ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች ፣ በያዝነው በጀት ዓመትም በመንግሥትና በበጎ ፈቃድ የተሠሩ ከ20 ሺህ በላይ ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መሸጋገራቸውን ከንቲባዋ ይፋ አድርገዋል፡፡
የኮልፌ፣ ሰሚት፣ ሐያትና ንፋስ ስልክ የገበያ ማዕከላት፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ፣ የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ ፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአብርሆት ቤተ-መፃህፍት እና የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት የከተማዋን ገጽታና የነዋሪዎቿን ሕይወት ከቀየሩት ፕሮጀክቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም የነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ የእንጀራ ፋብሪካዎች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና የልጆች መጫወቻዎች ተጠቃሽ ናቸው ፡፡
በዲዛይንና ግንባታ ዘርፍ 2 ሽሕ 064 ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ፥ ዕቅዱን በላቀ ሁኔታ በማሳካት 2 ሺህ 462 ግንባታዎችን ማጠናቀቅ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው አብራርተዋል ፡፡
በያለው ጌታነህ